ሰኔ 2, 2023
ስሎቫኪያ
የማቴዎስ መጽሐፍ በሮማኒ ቋንቋ ወጣ (የምሥራቅ ስሎቫኪያ)
ግንቦት 27, 2023 መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ መጽሐፍ በሮማኒ (የምሥራቅ ስሎቫኪያ) ቋንቋ ወጣ፤ የቼክ-ስሎቫክ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ያሮስላቭ ሴኬላ ይህን ምሥራች ያበሰረው በምሥራቃዊ ስሎቫኪያ በምትገኘው በሚኩላቭስካ በተደረገ ልዩ ስብሰባ ላይ ነው። በዚህ ልዩ ስብሰባ ላይ የተገኙ ሁሉ የመጽሐፉን የታተመ ቅጂ ማግኘት ችለዋል። መጽሐፉ በኤሌክትሮኒክ ቅጂም ተለቅቋል።
ሮማኒ እንደ ሂንዲ፣ ቤንጋሊና ፑንጃቢ ካሉት ቋንቋዎች ጋር ይቀራረባል። በሮማኒ ቋንቋ ውስጥ ያሉ በርካታ ቃላት የተወሰዱት የሮማኒ ሰዎች በሰፈሩባቸው ክልሎች ከሚነገሩ ቋንቋዎች ነው። ይህም በምሥራቃዊ ስሎቫኪያ የሚነገረው የሮማኒ ቀበልኛ ከሌሎቹ ብዙ የቃላት ልዩነት እንዲኖረው አድርጓል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ቡድኑ የትርጉም ሥራውን ባከናወነበት ወቅት ይህን ከግምት አስገብቷል።
በሮማኒ (የምሥራቅ ስሎቫኪያ) ቋንቋ የተዘጋጀ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አለ፤ ሆኖም ይህ ትርጉም ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም “ጌታ” እና “አምላክ” የሚል ትርጉም ባላቸው ኦ ራይ እና ኦ ዴል በሚሉት ስሞች ቀይሯቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ተርጓሚዎቹ በርካታ ጥቅሶች ላይ መልእክቱን እነሱ በመሰላቸው መንገድ አስፍረውታል፤ ይህም አንባቢዎች የጥቅሶቹን ትክክለኛ መልእክት መረዳት ከባድ እንዲሆንባቸው አድርጓል። አዲስ የወጣው የማቴዎስ መጽሐፍ ትርጉም ግን የይሖዋን ስም የያዘ ሲሆን የተጻፈውም በቀላሉ በሚገባ ቋንቋ ነው።
በትርጉም ሥራው ላይ የተካፈለ አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የአምላክን መልእክት በትክክል የሚያስተላልፍ መሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ሰዎች አምላክን ሊያውቁትና ሊወዱት የሚችሉት ይህ ከሆነ ብቻ ነው።”
ሌላ ተርጓሚም እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥቷል፦ “የሮማኒ ሰዎች ብዙ ጊዜ መድሎ የሚደረግባቸው ከመሆኑ አንጻር በተለይ ማቴዎስ 10:31 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በጣም ያጽናናቸዋል። ጥቅሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በኖሩ ሰዎች ዘንድ ያን ያህል ዋጋ የማይሰጣቸውን ድንቢጦችን እንኳ ይሖዋ እንደሚያስተውል ይናገራል። እኛ ደግሞ ለይሖዋ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አለን።”
ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አንባቢዎች ስለ ይሖዋ መማራቸውን እንዲቀጥሉ እንዲሁም አፍቃሪ አምላክ እንደሆነና እንደሚያስብላቸው እንዲገነዘቡ እንደሚረዳቸው ሙሉ እምነት አለን።—1 ጴጥሮስ 5:7