በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 20, 2021
ስሎቬንያ

የተሻሻለው “አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ” በስሎቬንያኛ ወጣ

የተሻሻለው “አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ” በስሎቬንያኛ ወጣ

ታኅሣሥ 18, 2021 የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በስሎቬንያኛ ወጣ። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ አስቀድሞ በተቀዳ ፕሮግራም አማካኝነት የመጽሐፍ ቅዱሱን መውጣት ያበሰረ ሲሆን ፕሮግራሙ 2,000 ገደማ ለሚሆኑ ሰዎች ተላልፏል። መጽሐፍ ቅዱሱ አሁን የሚገኘው በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ነው፤ የታተመው ቅጂ ደግሞ በ2022 ይወጣል።

መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ በስሎቬንያኛ የተተረጎመው በ1584 ነው። ዳልማቲን በመባል የሚታወቀው የመጀመሪያው ሙሉ የስሎቬንያኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የወጣው በዚያ ዓመት ነው። በዛሬው ጊዜ በውል የታወቁ 80 የሚያህሉ የዳልማቲን መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ብቻ ናቸው ያሉት፤ አንዱ የሚገኘው በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ባለው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ቤተ መዘክር ውስጥ ነው።

በ1925 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የሆነው ወንድም ፍራንዝ ብራንድ በሚሠራበት ፀጉር ቤት ውስጥ መስበክ ጀመረ፤ ፀጉር ቤቱ የሚገኘው በማሪቦር፣ ስሎቬንያ ነበር። በዚያው ዓመት፣ ጥቂት ሰዎች በቋሚነት እየተገናኙ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይወያዩ ጀመር። በ1930 በስሎቬንያ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በአገሪቱ ለሚካሄደው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ ድጋፍ ለማድረግ ሲሉ አንድ ቢሮ አቋቋሙ። ወንድሞቻችን ከትርጉም ሥራ ጋር በተያያዘ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ታሪካዊ ክንውን የአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በስሎቬንያኛ መውጣት ነው፤ የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ሳሙኤል ኸርድ በ2009 በሉብሊያና፣ ስሎቬንያ በተካሄደ አውራጃ ስብሰባ ላይ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መውጣቱን አበሰረ።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅትና በቀጣዮቹ ዓመታት፣ መጀመሪያ ላይ ናዚዎች በኋላም በአካባቢው ያሉ ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከባድ ስደት አድርሰውባቸዋል። በዚህ ወቅት በርካታ ወንድሞች ታስረዋል፤ አንዳንዶቹም ተገድለዋል። በ1953 ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ተጥሎ የነበረውን እገዳ ሲያነሱና በነፃነት አምልኳቸውን እንዲያከናውኑ ሲፈቅዱ ሁኔታው ተሻሻለ። በዛሬው ጊዜ በስሎቬንያ 1,757 አስፋፊዎች አሉ።

የስሎቬንያኛ ትርጉም ቡድን የሚኖረውና የሚሠራው በካምኒክ ከተማ በሚገኘው የስሎቬንያ ቤቴል ውስጥ ነው

በስሎቬንያ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ወንድም ሎሽ የመጽሐፍ ቅዱሱን መውጣት ባበሰረበት ፕሮግራም ላይ በተናገረው በሚከተለው ሐሳብ እንደሚስማሙ እርግጠኞች ነን፦ “ከዚህ አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ በመተዋወቅ ኃይሉን ጥሩ አድርጋችሁ ተጠቀሙበት! . . . [የተሻሻለው] አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በስሎቬንያኛ መውጣቱ ‘የታመነውን ቃል’ በጥብቅ መከተል እንድትችሉ ይረዳችኋል!”—ቲቶ 1:9