ታኅሣሥ 18, 2019
ስዊድን
ስዊድን የይሖዋ ምሥክሮች ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ እንደሆኑ ገለጸች
የስዊድን መንግሥት ከጥር 1, 2000 አንስቶ የሃይማኖታዊ ማኅበራት ድጋፍ በተባለው ሕግ መሠረት ለሃይማኖት ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ነው። የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ብቁ የሚሆኑት “የማኅበረሰቡን መሠረታዊ እሴቶች ለማጠናከርና ለማጎልበት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ” እንዲሁም “አዘውትረው ለማኅበረሰቡ መልካም ነገሮች የሚያደርጉ” የሃይማኖት ድርጅቶች ብቻ ናቸው።
ስዊድን ለአብዛኞቹ ሃይማኖቶች በሕግ የተደነገገውን የገንዘብ ድጋፍ የምታደርግ ቢሆንም የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ መሆናቸውን በመተቸት ከ2007 አንስቶ ድጋፉን ለእነሱ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነችም።
ወንድሞቻችን ሌላ ምርጫ ስላልነበራቸው የስዊድንን መንግሥት ለሦስት ጊዜ ያህል ፍርድ ቤት አቅርበውታል። በሦስቱም ጊዜያት የጠቅላይ አስተዳደሩ ፍርድ ቤት፣ መንግሥት ለድርጅታችን ገንዘብ በመከልከል የወሰደው እርምጃ ሕጉን የሚጻረር እንደሆነና መስተካከል እንዳለበት ገልጿል።
በመጨረሻም ጥቅምት 24, 2019 የስዊድን መንግሥት ውሳኔውን የቀየረ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ ምሥክሮች መንግሥት የደነገገውን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት “ሁሉንም ሕጋዊ ብቃቶች ያሟላሉ” በማለት ተናግሯል።
በቅርቡ በኖርዌይ ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞ ነበር፤ የኖርዌይ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ ለሁሉም ሃይማኖቶች በቋሚነት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል። ይሁንና ከጥቂት ወራት ወዲህ የኖርዌይ መንግሥት ለይሖዋ ምሥክሮች ድጋፍ ማድረግ ይኖርበት እንደሆነ እንደገና እንዲያጤን ተጠይቆ ነበር፤ ይህ የሆነው በፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ በመሆናችን ነው። ወንድሞችም በምላሹ ከፖለቲካ ገለልተኝነት ጋር በተያያዘ ያለንን አቋም አስመልክቶ ትክክለኛ መረጃ ለኖርዌይ ባለሥልጣናት አቀረቡ። ከዚህም ሌላ ወንድሞቻችን የስዊድን ጠቅላይ አስተዳደር ፍርድ ቤት እንደፈረደልን የሚገልጽ ሰነድ እንዲሁም በጀርመንና በጣሊያን ፍርድ ቤቶችና አስተዳደር አካላት በተነሱ ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ለእኛ እንደተፈረደልን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ለባለሥልጣናቱ አቅርበዋል።
ኅዳር 18, 2019 የኖርዌይ ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮች በሕግ የተደነገገውን የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት እንዳለባቸው ገልጸዋል፤ እንዲህ ብለዋል፦ “በምርጫ መሳተፍ የኖርዌይ ዜጎች መሠረታዊ መብት እንጂ ግዴታ አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ይህን መብት ላለመጠቀም መርጠዋል። . . . [መንግሥት ግን] ይህን ሁኔታ ሕግ የፈቀደላቸውን የገንዘብ ድጋፍ ለመከልከል የሚያበቃ ሕጋዊ መሠረት አድርጎ ሊጠቀምበት አይገባም።”
በስካንዲኔቪያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግለው ወንድም ዳግ ኤሪክ ክሪስቶፈርሰን እነዚህን ውሳኔዎች በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “መንግሥት ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ ነገር እንደምናከናውን መግለጹ አስደስቶናል። እንዲህ ያለ ዝግጅት ያላቸው ሌሎች አገሮችም ይህን ውሳኔ ልብ እንደሚሉት ተስፋ እናደርጋለን።” ከሁሉ በላይ ደግሞ ታላቅ ሕግ ሰጪ የሆነውን ይሖዋን እናመሰግነዋለን።—ኢሳይያስ 33:22