በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ እንግዶች አውደ ርዕዩን ሲጎበኙ። መሃል ላይ፦ በባርሴሎና፣ ስፔን የሚገኘው የላ ሞዴሎ መግቢያ። በስተ ቀኝ፦ አንድ ወንድም እስር ቤት ሆኖ ለሚስቱ የጻፋቸውን ደብዳቤዎች ቅጂዎች ማሳያ።

ታኅሣሥ 5, 2023
ስፔን

ስፔን ውስጥ “በሕሊናቸው ምክንያት የታሰሩ” የይሖዋ ምሥክሮችን ታሪክ የሚያወሳ ልዩ አውደ ርዕይ ተዘጋጀ

ስፔን ውስጥ “በሕሊናቸው ምክንያት የታሰሩ” የይሖዋ ምሥክሮችን ታሪክ የሚያወሳ ልዩ አውደ ርዕይ ተዘጋጀ

አንዲት እህት የቀድሞውን ላ ሞዴሎ ማረሚያ ቤት ለእንግዶች ስታስጎበኝ

ከጥቅምት 14 እስከ ታኅሣሥ 16, 2023 “በሕሊናቸው ምክንያት የታሰሩ” በሚል ርዕስ አዲስ አውደ ርዕይ ለእይታ ቀርቦ ነበር፤ አውደ ርዕዩ የተዘጋጀው ባርሴሎና፣ ስፔን ውስጥ በሚገኝ ሙዚየም እና የባሕል ማዕከል ሲሆን ቦታው ከዚህ ቀደም ላ ሞዴሎ በመባል የሚታወቅ ማረሚያ ቤት ነበር። አራት ክፍሎች ያሉት የዚህ አውደ ርዕይ ዓላማ፣ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን ለማላላት ፈቃደኛ ያልሆኑ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ስላሳዩት ጠንካራ እምነት ለማኅበረሰቡ ማሳወቅ ነው፤ ይህ የመንግሥት ባለሥልጣናትንና ምሁራንንም ይጨምራል።

አውደ ርዕዩ፣ የጦር ሠራዊቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ከ1930ዎቹ አንስቶ የታሰሩ ወንድሞቻችንን ታሪክ የሚያወሳ ነው። በ1960ዎቹ እና በ1970ዎቹ ዓመታት፣ የታሰሩት ወንድሞች ቁጥር 1,000 ገደማ ደርሶ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ ከ40 በላይ የሚሆኑት የታሰሩት በላ ሞዴሎ ማረሚያ ቤት ነበር።

ከዚህ ቀደም በሕሊናቸው ምክንያት የታሰሩትን የሚያሳዩ በአውደ ርዕዩ ላይ የቀረቡ ምስሎች

በአውደ ርዕዩ ላይ የታዩት ትዕይንቶች ወንድሞች የጦር ሠራዊቱን ለመቀላቀል ፈቃደኛ ያልሆኑት ለምን እንደሆነና ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በእስር ቤት ውስጥ ያሳለፉት ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር አስቃኝተዋል። እነዚህ ታማኝ ወንድሞች ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በድፍረት የወሰዱት አቋም ለውጥ አምጥቷል፤ በ1984 የስፔን መንግሥት፣ በሕሊና ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ያለመስጠት መብትን በይፋ አጸደቀ።

የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ሚጌል አንሄል ፕላሳ በአውደ ርዕዩ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር እንዲያቀርቡ ተጋብዘው ነበር። ፕሮፌሰሩ በላ ሞዴሎ ታስረው የነበሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮችን የማነጋገር አጋጣሚ አግኝተዋል። የወንድሞችን ሁኔታ ጠቅለል አድርገው ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “አንዳቸውም ቢሆኑ በላ ሞዴሎ ስላሳለፉት ሁኔታ ምንም ዓይነት አሉታዊ ሐሳብ አልሰጡም፤ ስለ እስር ቤት ጠባቂዎቹም እንኳ መጥፎ ነገር አልተናገሩም። በእስር ቤቱ ስላሳለፉት ሁኔታ ሲናገሩ ሁሉም ፊት ላይ ፈገግታ ይታይ ነበር።” በላ ሞዴሎ ታስሮ የነበረ ፈርናንዶ ትሬፓት የተባለ ወንድምም በፕሮግራሙ ላይ ተገኝቶ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ከ50 ዓመታት በኋላም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛውን ውሳኔ እንዳደርግ እንደረዳኝ ሙሉ እምነት አለኝ። አሁንም ቢሆን ተመሳሳይ ውሳኔ ማድረጌ አይቀርም።”

ፕሮግራሙን ያስተባበረው ወንድም ዳቪድ ባይዴስ እንዲህ ብሏል፦ “አውደ ርዕዩ፣ ያለፈ ታሪክን የሚያወሳ ቢሆንም ርዕሰ ጉዳዩ በዛሬው ጊዜም ትኩረት የሚያሻው ነው። በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አገራት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተ እምነታቸው ምክንያት የታሰሩ 200 ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ።”

በላ ሞዴሎ በተዘጋጀው ልዩ አውደ ርዕይ ላይ በአስጎብኚነት የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች

በስፔን የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለበርካታ ዓመታት ላሳዩት ታማኝነትና ጽናት ከፍተኛ አድናቆት አለን፤ በአሁኑ ጊዜ በእምነታቸው ምክንያት ለታሰሩትም መጸለያችንን እንቀጥላለን።—ዕብራውያን 13:3