በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የስፔን ሕግ አውጪ ምክር ቤት የሚሰበሰብበት ሕንፃ፣ ማድሪድ፣ ስፔን

ግንቦት 24, 2023
ስፔን

ስፔን የይሖዋ ምሥክሮችን ከግብር ነፃ የሚያደርግ ታሪካዊ ውሳኔ አሳለፈች

ስፔን የይሖዋ ምሥክሮችን ከግብር ነፃ የሚያደርግ ታሪካዊ ውሳኔ አሳለፈች

ሚያዝያ 26, 2023 የስፔን መንግሥት በአገሪቱ የግብር ሕግ ላይ ጉልህ ማሻሻያ አጽድቋል። ውሳኔው ለስፔን የይሖዋ ምሥክሮች አዎንታዊ ገጽታዎች አሉት።

ይህ የመንግሥት ውሳኔ፣ ድርጅታችን በመላ አገሪቱ ባሉት ቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎች ላይ ከንብረት ግብር ነፃ እንዲሆን ያደርጋል። ለይሖዋ ምሥክሮች ሥራ መዋጮ የሚያደርጉ ግለሰቦችም ከመዋጮዋቸው ላይ ግብር መክፈል እንዳይኖርባቸው ያደርጋል። በተጨማሪም ይህ ማስተካከያ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በደነገገው መሠረት “እውቅና ከተሰጠው ሃይማኖት” የሚጠበቀውን መሥፈርት እንደሚያሟሉ ያረጋግጣል።

የስፔን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካይ የሆነው ወንድም ጆን ኮማስ (በስተ ግራ)፣ የፕሬዚዳንቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን ከሆኑት ከአቶ ፌሊክስ ቦላኞስ (በስተ ቀኝ) ጋር

የስፔን የይሖዋ ምሥክሮች፣ በሚገባ የሚታወቅ የሃይማኖት ድርጅት ተብለው ሕጋዊ እውቅና የተሰጣቸው ሰኔ 2006 ነው፤ ያም ቢሆን ሌሎቹን የአገሪቱን ሃይማኖቶች ከግብር ነፃ ከሚያደርገው ዝግጅት ተጠቃሚ አልነበሩም። ወንድሞቻችን፣ ሃይማኖታዊ ድርጅታችን ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ እንዲሆን አቤቱታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ከዚያም ባልተጠበቀ ሁኔታ ሚያዝያ 24, 2023 የፕሬዚዳንቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናት የስፔን የይሖዋ ምሥክሮች ተወካዮችን ለስብሰባ ጠሯቸው። አትራፊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በሚመለከተው የግብር ሕግ ላይ ማሻሻያ ሊደረግ እንደሆነና የይሖዋ ምሥክሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታሰቡን ለወንድሞች ነገሯቸው። ከሁለት ቀናት በኋላ ማለትም ሚያዝያ 26, 2023 የስፔን ሕግ አውጪ ምክር ቤት በግብር ሕጉ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ አጸደቀው። ማሻሻያው ከሰኔ 2023 አንስቶ በይፋ ሥራ ላይ እንደሚውል ይጠበቃል።

ይህ ጉልህ ውሳኔ የስፔን የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ነፃነት እንዲከበር ትልቅ ሚና አለው፤ ይህ በመሆኑም በጣም ተደስተናል።—ፊልጵስዩስ 1:7