በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ግንቦት 27, 2020
ስፔን

በስፔን የሚኖሩ ባልና ሚስት ከአንዲት ነርስ የምስጋና ደብዳቤ ደረሳቸው

በስፔን የሚኖሩ ባልና ሚስት ከአንዲት ነርስ የምስጋና ደብዳቤ ደረሳቸው

አሁን በተከሰተው ወረርሽኝ የተነሳ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ተስፋ ሰጪ ደብዳቤዎች በመጻፍ ጎረቤቶቻቸውን ለማጽናናት ጥረት እያደረጉ ነው። ወንድም ሆስዌ ላፖርታ እና ባለቤቱ ቫኔሳ በባርሴሎና፣ ስፔን በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ላሉ የሕክምና ባለሙያዎች እና በኮቪድ-19 የተያዙ ታካሚዎች የሚያጽናኑ ደብዳቤዎችን ጽፈው ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት ከአንዲት ነርስ የምስጋና ደብዳቤ ተልኮላቸው ነበር። ነርሷ በደብዳቤው ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎች ተደርገው ደብዳቤው ይፋ እንዲሆን ፈቃድ ሰጥታለች፤ ደብዳቤው ከዚህ በታች ቀርቧል። a

እኔ ነርስ ነኝ፤ . . . ይህን ደብዳቤ የምጽፈው የ97 ዓመት አረጋዊትና አያት የሆኑትን [ስማቸው ተሰርዟል] በመወከል ነው። ደብዳቤያችሁን ያነበብኩላቸው ዛሬ ጠዋት ነው። ደብዳቤዎች ለታካሚዎች የሚደርሱበት የተደራጀ አሠራር የለም፤ ይህ ደብዳቤ እኔ እጅ የገባው ግን በአጋጣሚ አይመስለኝም። ምክንያቱም ደብዳቤው ቢያንስ ሁለት ሰዎች ማለትም እኔና [ታካሚዋ] . . . ተስፋ እንዳለን እንድንገነዘብ ረድቶናል። [ታካሚዋ] በቅርቡ እንደሚሞቱ የሚጠበቁ አረጋዊት ናቸው፤ ሆኖም ከመሞታቸው በፊት ለሆስዌ የሚከተለውን ጥያቄ ማቅረብ እንደሚፈልጉ ነግረውኝ ነበር፦ “በ97 ዓመቴ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው ተስፋ ተጠቃሚ መሆን እችላለሁ?”

ዛሬ ጠዋት አሥር ደቂቃ ወስጄ ከጠቀሳችሁት ድረ ገጽ ላይ አንድ ሐሳብ አንብቤላቸው ነበር። ሳነብላቸው ዓይናቸው በራ እንዲሁም ስሜታቸው ተነካ። ፊታቸው ላይ የደስታና የሰላም ስሜትም ይነበብ ነበር፤ እንዲህ ያለ ስሜት ከተሰማቸው ረጅም ጊዜ ሆኗቸው ነበር። ከዚያም “ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው?” የተባለውን ቪዲዮ አየን።

ስለ ውጥረት የሚናገረውን [“ንቁ!”] መጽሔትም አንብቤ ነበር፤ አሁን ያለው ሁኔታ ያስከተለብንን ውጥረት ለመቋቋም ረድቶኛል። እንደምታውቁት አሁን ያለንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው።

እዚህ የሚሠሩት የሕክምና ባለሙያዎች የሚያማክሩት የሥነ ልቦና ባለሙያ የላቸውም፤ እናንተ የሰጣችሁን መረጃ ግን በማንኛውም ሰዓት ስለሚገኝ ልናሰላስልበት እንችላለን። ወረርሽኙ ሲያልፍ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ማወቅ እፈልጋለሁ፤ እናንተም ማወቅ ያለብኝን ነገር ለማስተማር ዝግጁ እንደምትሆኑና አዲስ ዓለም እንደሚመጣ እንድተማመን እንደምትረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ። የላካችሁት ደብዳቤ በዚያ ቀን፣ በዚያች ሰዓት በመድረሱና ደብዳቤውን [ለታካሚዋ] ማድረስ በመቻሌ አምላክን በጣም አመሰግነዋለሁ!

ለእናንተም ሆነ ለቤተሰባችሁ መልካም ጤንነት እመኝላችኋለሁ፤ ተስፋችሁ ይህን ሁኔታ ከእኛ በተሻለ መንገድ ለመቋቋም እንደሚረዳችሁ እርግጠኛ ነኝ። ጊዜያችሁን መሥዋዕት በማድረግ እንደ እኔና እንደ [ታካሚዋ] ያሉ ሰዎችን ስለምትረዱ አመሰግናችኋለሁ። ባንተዋወቅም እንኳ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ውስጥ ተሰምቶን የማያውቅ የደስታ ስሜት እንዲሰማን አድርጋችኋል።

ልባዊ ምስናጋዬ ይድረሳችሁ።

እንደዚህ ያሉ የአድናቆት ደብዳቤዎች በዚህ ወረርሽኝ ወቅት መስበካችንን እንድንቀጥል ያነሳሱናል። በአገልግሎታችን የምንጠቀምባቸው ቃላት ለሌሎች የመጽናኛ ምንጭ እንዲሆኑ እንጸልያለን።—ምሳሌ 15:23

a ደብዳቤው የተጻፈው በስፓንኛ ነበር።