ኅዳር 6, 2024
ስፔን
በስፔን ደቡብ ምሥራቃዊ ክልል አውዳሚ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከሰተ
ጥቅምት 29, 2024 በስፔን ደቡብ ምሥራቃዊ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ በጣለው ዶፍ ዝናብ ምክንያት በጎርፍ ተጥለቅልቀዋል። ቫሌንሲያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ለስምንት ሰዓታት የጣለው ዝናብ መጠን፣ ወትሮ በአካባቢው በአንድ ዓመት ውስጥ ከሚጥለው ጋር ተመጣጣኝ ነው። ለምሳሌ በቱሪስ ከተማ የዘነበው ዝናብ 64 ሴንቲ ሜትር ደርሷል። በጎርፍ መጥለቅለቁና ከመሬት መንሸራተት የተነሳ ብዙ ከተሞች በጭቃ ተሸፍነዋል፤ መንገዶችና ድልድዮችም በጎርፍ ተወስደዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለምግብ፣ ያለውኃና ያለኤሌክትሪክ አቅርቦት ቀርተዋል። ቢያንስ 217 ሰዎች ሞተዋል፤ ሌሎች ብዙዎች ደግሞ የደረሱበት አይታወቅም።
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
የሚያሳዝነው፣ አንዲት የ77 ዓመት እህት ሕይወታቸውን አጥተዋል
19 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል
1 ቤት ወድሟል
21 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
27 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል
157 አስፋፊዎች የግል ተሽከርካሪዎቻቸው በጎርፍ ተወስደውባቸዋል
3 የስብሰባ አዳራሾች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
የእርዳታ እንቅስቃሴ
የቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች እና የአካባቢው ሽማግሌዎች መንፈሳዊ ማጽናኛና ስሜታዊ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ ቁሳዊ እርዳታ እያቀረቡ ነው
የእርዳታ ሥራውን የሚያስተባብር የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል
አደጋው ባልደረሰባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች፣ ጎርፉ ካጠቃቸው አካባቢዎች የሚመጡ የእምነት አጋሮቻቸውን በጊዜያዊነት ለመቀበል ቤታቸውን ክፍት በማድረግ ፍቅራቸውን እያሳዩ ነው
በስፔን በተከሰተው አውዳሚ የጎርፍ መጥለቅለቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ሁሉ ከልባችን እናዝናለን። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋን ብርታታቸውና ኃይላቸው የሚያደርጉ ሁሉ በጭንቅ ጊዜ ‘ምንም የሚያስፈራቸው ነገር እንደማይኖር’ የሚሰጠው ዋስትና ያጽናናል።—ኢሳይያስ 12:2