በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስፔን ቅርንጫፍ ቢሮ የትርጉም ሥራው የሚከናወንበት በቅርቡ የታደሰው ሕንፃ

መስከረም 19, 2022
ስፔን

የስፔን ቅርንጫፍ ቢሮ እድሳት ለትርጉም ሥራው ከፍተኛ እገዛ አድርጓል

የስፔን ቅርንጫፍ ቢሮ እድሳት ለትርጉም ሥራው ከፍተኛ እገዛ አድርጓል

በስፔን ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ከሚገኙት የቢሮ ሕንፃዎች የአንዱ እድሳት በቅርቡ ተጠናቅቋል። ይህን ሕንፃ በዋነኝነት የሚጠቀምበት የትርጉም ክፍሉ ነው። ይህ እድሳት በ2025 እንደሚጠናቀቅ የሚታሰበው ሰፊ የቅርንጫፍ ቢሮ እድሳት ክፍል ነው።

የታደሰው ሕንፃ እስከ 4,000 የሚደርሱ የትርጉም የማመሣከሪያ ጽሑፎችን የያዘ ቤተ መጻሕፍት አለው። ቤተ መጻሕፍቱ በኤሌክትሮኒክ ቅጂ የማይገኙ መጻሕፍትን አካትቷል።

የስፔን ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆን በርስናል እንዲህ ብሏል፦ “በስፔን ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር የሚከናወነው ሥራ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ታይቶበታል። ቀደም ሲል ቅርንጫፍ ቢሯችን በዋነኝነት የሚያገለግለው ለማተሚያና ለመጋዘንነት ነበር፤ አሁን ግን የስፓንኛና የስፓንኛ የምልክት ቋንቋ ትርጉም የሚካሄደው እንዲሁም በበርካታ የአውሮፓ ቋንቋዎች ብሬይል የሚዘጋጀው በቅርንጫፍ ቢሯችን ውስጥ ነው። በመሆኑም ቢሮዎቹን ማስፋት አስፈልጎናል። ይህ እድሳት ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበራችን የተሻለ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያስችለን ምንም ጥርጥር የለውም።”

በአራቱ የመኖሪያ ሕንፃዎች ላይ የሚካሄደው እድሳትም ተጀምሯል። በሥራው እስከ 200 የሚደርሱ የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ይካፈላሉ። ለሠራተኞቹ የሚሆኑ 70 ጊዜያዊ መኖሪያ ቤቶች ቅርንጫፍ ቢሮው ግቢ ውስጥ እየተዘጋጁ ነው።

ቀጣዩ የእድሳት ሥራ ሲከናወን ለፈቃደኛ ሠራተኞቹ የሚሆኑ ጊዜያዊ መኖሪያ ቤቶች ወደ ስፔን ቅርንጫፍ ቢሮ ተወስደዋል

በስፔን ሥራችን እያደገ ነው። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 120,530 አስፋፊዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ 23,565ቱ በዘወትር አቅኚነት ያገለግላሉ፤ ስፔን ባለፈው የአገልግሎት ዓመት ውስጥ በሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ቁጥር ላይ ስምንት ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር አስመዝግባለች።

ይሖዋ፣ እነዚህ ሕንፃዎች የእሱን ቅዱስ ስም ማስከበር እንዲችሉ የማስፋፊያ ሥራውን እንደሚባርከው እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 61:8