በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 8, 2020
ቡልጋሪያ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በቡልጋሪያ ላሉ የይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በቡልጋሪያ ላሉ የይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

ኅዳር 10, 2020 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የቡልጋሪያ መንግሥት የወንድሞቻችንን የሃይማኖት ነፃነት መብት እንደተጋፋ የሚገልጽ ውሳኔ አስተላለፈ። በዚህ ውሳኔ መሠረት ባለሥልጣናቱ በቫርና፣ ቡልጋሪያ የተጀመረው የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ እንዲቀጥል ሊፈቅዱ ይገባል። ከአሥር ዓመት በላይ በዘለቀው ተቃውሞ ምክንያት የግንባታ ሥራው ተቋርጦ ነበር። በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ቡልጋሪያ ለወንድሞቻችን 9,600 ዩሮ (11,500 የአሜሪካ ዶላር) ካሳ እንድትከፍል አዟል።

የፍርድ ቤቱ ሂደት የተጀመረው ወንድሞቻችን ጥር 2006 በገዙት መሬት ላይ ከሚገነቡት የስብሰባ አዳራሽ ጋር በተያያዘ ነበር። በቫርና ያሉት የመንግሥት ባለሥልጣናት ግንቦት 2007 ላይ የግንባታ ፈቃድ የሰጡ ሲሆን ወንድሞቻችንም ወዲያውኑ ግንባታውን ጀመሩ። ሆኖም በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ከንቲባው የግንባታ ሕጎች እንደተጣሱ በመግለጽ ሥራው እንዲቆም አዘዘ። በዚያው ወር፣ በስፋት የሚታወቅ የቡልጋሪያ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ከሌሎች ብዙ ሰዎች ጋር በመሆን የግንባታ ቦታው ላይ ፖስተሮችን ይዘው የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ።

የቫርና ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክሮችን ስም የሚያጠፋ መግለጫ ማውጣታቸውን እንዲሁም “ለተቃዋሚዎቹ ሙሉ ድጋፍ” እንደሚሰጡ መናገራቸውን የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤቱ ገልጿል። ከንቲባውም ቢሆን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ ላይ ተቃውሞውን እንደሚደግፍ ተናግሯል።

ከንቲባውም ሆነ ሌሎች ባለሥልጣናት ግንባታውን ያገዱት በጥላቻ ተነሳስተው እንደሆነ የሚያሻማ አልነበረም። እነሱ ግን እንዲህ ያደረጉት በሃይማኖታዊ ጥላቻ ሳይሆን ከግንባታ ሕጎች ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ውዝግብ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።

ወንድሞቻችን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ጨምሮ በቡልጋሪያ ላሉ በርካታ ፍርድ ቤቶች ይግባኝ ቢጠይቁም ምንም ውጤት አላገኙም። በዚህ መሃል ለተወሰነ ጊዜ ያህል፣ በቫርና ያለው ጉባኤ ስብሰባዎችን ለማድረግ ሌላ ቦታ ለመከራየት ተገዶ ነበር።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ባለሥልጣናቱ የፈጸሙት ድርጊት መሠረተ ቢስ እንደሆነ አስታውቋል። ፍርድ ቤቱ የቫርና ባለሥልጣናት የስብሰባ አዳራሹ ግንባታ እንዲቆም ያስተላለፉት ትእዛዝ በአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ አንቀጽ 9 እና 11 ላይ የተገለጸውን “የሐሳብ፣ የሕሊና እና የሃይማኖት ነፃነት” እንደሚጥስ ስድስት ለአንድ በሆነ ድምፅ ወስኗል።

ወንድሞቻችን ባለሥልጣናቱ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ የግንባታ ሥራው እንዲቀጥል እንደሚፈቅዱ ተስፋ ያደርጋሉ፤ በቫርና ከተማ የሚገነባው ይህ የአምልኮ ቦታ ማኅበረሰቡን የሚጠቅም ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ ስም እንዲከበር ያደርጋል። ይሖዋ ሁልጊዜም ከጎናችን በመሆን ስለሚረዳን እናመሰግነዋለን።—መዝሙር 54:4