በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጋቢት 24, 2023
ቡርኪና ፋሶ

አዲስ ዓለም ትርጉም በሙር ቋንቋ ወጣ

አዲስ ዓለም ትርጉም በሙር ቋንቋ ወጣ

መጋቢት 19, 2023 አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሙር ቋንቋ ወጣ! የቤኒን ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዩሱፍ ኦድራጎ ይህን ያበሰረው በቡርኪና ፋሶ ዋና ከተማ በዋጋዱጎ በተካሄደ ፕሮግራም ላይ ነው። a በሌሎች ከተሞች የሚገኙ በርካታ ታዳሚዎች ፕሮግራሙን በቀጥታ ስርጭት ተከታትለዋል። በአጠቃላይ 1,730 ሰዎች ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተዋል። የመጽሐፍ ቅዱሱ መውጣት ከተገለጸ በኋላ፣ ፕሮግራሙ ላይ በአካል ለተገኙት ታዳሚዎች የታተመው ቅጂ ተሰጥቷቸዋል፤ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት የተዘጋጀውም ለተጠቃሚዎች ተለቅቋል።

ሙር፣ ቡርኪና ፋሶ ውስጥ በስፋት የሚነገረው ቋንቋ ነው፤ የስምንት ሚሊዮን ገደማ ሰዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው። በአጎራባች አገራት ይኸውም በማሊ፣ በሴኔጋል፣ በቶጎ፣ በኮት ዲቩዋርና በጋናም ይነገራል።

የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ በቡርኪና ፋሶ ወደሚነገር ቋንቋ ሲተረጉሙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው። በሙር ቋንቋ የተዘጋጁ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች ቢኖሩም አንዳቸውም ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም አይጠቀሙም።

አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “እንደ ምሳሌ እና መኃልየ መኃልይ ያሉትን የግጥም ይዘት ያላቸው መጻሕፍት መተርጎም ከባድ ነበር፤ ምክንያቱም በሙር ቋንቋ እንዲህ ያለው የአጻጻፍ ስልት የተለመደ አይደለም። እነዚህን መጻሕፍት ከተረጎምናቸው በኋላ ግን መልእክታቸው ምን ያህል ለመረዳት ቀላል እንደሆነ ስናይ በጣም ተደሰትን!”

የሙር ቋንቋ ተናጋሪ ወንድሞቻችን ከይሖዋ ባገኙት በዚህ ስጦታ የደስታቸው ተካፋይ ነን።—ያዕቆብ 1:17

a በቡርኪና ፋሶ የሚከናወነውን ሥራ የሚከታተለው የቤኒን ቅርንጫፍ ቢሮ ነው።