በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በ2019 የተከሰተው የዶሪያን አውሎ ነፋስ ባሃማስ ውስጥ በግሬት አባኮ ደሴት ላይ የሚገኘውን ብቸኛ የስብሰባ አዳራሽ አውድሞት ነበር። ዳግመኛ የተገነባው የስብሰባ አዳራሽ በቅርቡ ለይሖዋ አገልግሎት ተወስኗል

ጥር 26, 2023
ባሃማስ

ባሃማስ ውስጥ ዳግመኛ የተገነባው የስብሰባ አዳራሽ ለይሖዋ አገልግሎት ተወሰነ

ባሃማስ ውስጥ ዳግመኛ የተገነባው የስብሰባ አዳራሽ ለይሖዋ አገልግሎት ተወሰነ

ወንድም ማርክ ሳንደርሰን የውሰና ንግግር ሲሰጥ

የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ማርክ ሳንደርሰን ጥር 7, 2023 ባሃማስ ውስጥ በግሬት አባኮ ደሴት ላይ ዳግመኛ የተገነባውን የስብሰባ አዳራሽ ለይሖዋ አገልግሎት ወስኗል። አዳራሹ መስከረም 2019 በተከሰተው የዶሪያን አውሎ ነፋስ የተነሳ ወድሞ ነበር። የግንባታ ሥራውን መጋቢት 2020 ለማጠናቀቅ ታስቦ ነበር፤ ሆኖም ሊጠናቀቅ ሦስት ሳምንት ሲቀረው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሥራው ተገታ። የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሥራውን ለማጠናቀቅ የተመለሱት በ2021 ነው።

ወንድም ሳንደርሰን የውሰና ንግግሩን በሰጠበት ወቅት ሞቅ ባለ መንፈስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አውሎ ነፋሱ ብዙ ንብረታችሁን ጠራርጎ ወስዶባችሁ ይሆናል፤ እምነታችሁን ግን አልነጠቃችሁም። ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድናም አልነካባችሁም።”

አውሎ ነፋስ መቋቋም እንዲችል ተደርጎ የተገነባው አዲስ ሕንፃ በደሴቲቱ ላይ ብቸኛው የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ ነው፤ በእንግሊዝኛና በሄይቲኛ ክሪኦል በሚመሩ ሁለት ጉባኤዎች ውስጥ የታቀፉ 49 አስፋፊዎች አዳራሹን ይጠቀሙበታል። በውሰና ፕሮግራሙ ላይ 175 ሰዎች በአካል ተገኝተዋል፤ ሌሎች 167 ሰዎች ደግሞ ፕሮግራሙን በኢንተርኔት ተከታትለዋል። የውሰና ፕሮግራሙ የጉብኝት ፕሮግራምም ያካተተ ነበር፤ ጉብኝቱ የይሖዋ ምሥክር ለሆኑም ላልሆኑም ነዋሪዎች ክፍት ነበር።

ወንድም ጄክ ማጁሬ ወረርሽኙ የእርዳታ እንቅስቃሴውን በገታበት ወቅት የግንባታ ፈቃደኛ ሆነው ካገለገሉት ወንድሞች አንዱ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ነበር ያዘንነው። የቤቶቹ የጥገና ሥራ በማይታመን ፍጥነት እየተጠናቀቀ ነበር፤ ዳግመኛ የተገነባው የስብሰባ አዳራሽ ለመታሰቢያው በዓል ይደርሳል የሚል ተስፋም ነበረን፤ በኋላ ግን ሁሉ ነገር ቆመ።” ወንድም ጄክ በ2021 ወደ ፕሮጀክቱ ተመልሶ የስብሰባ አዳራሹንና ሌሎቹን ቤቶች ለመጠገን በሚከናወነው ሥራ ማገዝ ችሏል።

የአዳራሹ የውሰና ፕሮግራም በጣም አስደሳች ነበር

ወንድም ሳንደርሰን እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ለይሖዋ ሕዝቦች ትልቅ ምሥክርነት ነው፤ ምን ያህል ተባብረን እንደምንሠራና እንደምንዋደድ በግልጽ ታይቷል። በጥር ወር 2023 እዚህ በአካል ተገኝቼ ሕንፃው ቆሞ ማየቴና በወንድሞች ፊት ላይ የሚነበበውን ደስታ መመልከቴ ልዩ ስሜት ነው የፈጠረብኝ።”

ዳግመኛ የተገነባው ይህ አዲስ የስብሰባ አዳራሽ ለይሖዋ አምላካችን ታላቅ ውዳሴ እንደሚያመጣ እንተማመናለን።—ዕዝራ 3:10