ሰኔ 3, 2022
ቤኒን
የማቴዎስ ወንጌል በፎን ቋንቋ ወጣ
ግንቦት 29, 2022 መጽሐፍ ቅዱስ—የማቴዎስ ወንጌል በፎን ቋንቋ መውጣቱን የቤኒን ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሲልቫ ቦይስ አብስሯል። የዚህ መጽሐፍ ኤሌክትሮኒክ ቅጂ እንደወጣ የተገለጸው አስቀድሞ በተቀረጸ ፕሮግራም አማካኝነት ሲሆን 7,000 ያህል አስፋፊዎችና ለእውነት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። የታተመው የመጽሐፉ ቅጂ እስከ ታኅሣሥ 2023 እንደሚደርስ ይጠበቃል።
ይህ መጽሐፍ ከመውጣቱ በፊትም ቢሆን በፎን ቋንቋ የተተረጎሙ መጽሐፍ ቅዱሶች ማግኘት ይቻል ነበር። ሆኖም እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሶች የአምላክን ስም ከቃሉ ውስጥ አውጥተውታል፤ የበኩረ ጽሑፉን ሐሳብ በትክክል የማያስተላልፉ ብዙ አገላለጾችም አሏቸው። ከዚህም ሌላ ውድ ናቸው፤ እንዲያውም አንዳንድ መጻሕፍት ሻጮች ለይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ለመሸጥ ፈቃደኞች አይደሉም።
በቅርቡ የወጣው የማቴዎስ ወንጌል፣ የበኩረ ጽሑፉን ሐሳብ በትክክል ያስተላልፋል። ለምሳሌ ማቴዎስ 10:28 “ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ” ይላል። የዚህ ጥቅስ የግርጌ ማስታወሻ “ነፍስ” የሚለው የግሪክኛ ቃል “የወደፊት ሕይወት ተስፋን” እንደሚያመለክት ይገልጻል። አስፋፊዎች በአገልግሎት ላይ የሚያገኟቸውን ሰዎች እንደነዚህ ባሉት የመጽሐፉ ገጽታዎች ተጠቅመው መርዳት ይችላሉ።
የቤኒን ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ፓሌ ጄሬ እንዲህ ብሏል፦ “በጽሑፎቻችን ላይ የማቴዎስ መጽሐፍ ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል። የማቴዎስን ወንጌል ትክክለኛ ትርጉም ማግኘታችን ምሥራቹን ስንሰብክና ስናስተምር በጣም ይጠቅመናል። ይህን መጽሐፍ እንድናገኝ ስለረዳን ይሖዋን እናመሰግነዋለን! የትርጉም ቡድኑም ላከናወነው ሥራ አመስጋኞች ነን።”
የፎን ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ይህን መጽሐፍ ማግኘታቸው የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት በጣም እንደሚጠቅማቸው እንተማመናለን።—ማቴዎስ 5:3