በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሃሚልተን ቪዬራ በምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ እየታገዘ በብራዚል የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱን ሲያበስር፤ አድማጮች ደስታቸውን ሲገልጹ

መስከረም 26, 2022
ብራዚል

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በብራዚል የምልክት ቋንቋ ወጣ

ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በብራዚል የምልክት ቋንቋ ወጣ

የብራዚል ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሃሚልተን ቪዬራ እሁድ፣ መስከረም 18, 2022 ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በብራዚል የምልክት ቋንቋ እንደወጣ አብስሯል፤ መጽሐፍ ቅዱሱን jw.org እና JW Library Sign Language የተባለው አፕሊኬሽን ላይ ማግኘት ይቻላል። ከብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ የስብሰባ አዳራሽ የተላለፈውን ፕሮግራም ከ36,300 የሚበልጡ ሰዎች በቀጥታ ተከታትለውታል።

ወንድሞችና እህቶች በብራዚል የምልክት ቋንቋ የወጣውን መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው ፎቶግራፍ ሲነሱ

በብራዚል የምልክት ቋንቋ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ሲወጣ ይህ የመጀመሪያው ነው፤ በመላው ዓለምም ቢሆን ሦስተኛው ሙሉ የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የትርጉም ሥራው የጀመረው በ2006 በማቴዎስ ወንጌል ነው። ከዚያ በኋላ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ትርጉም ሲጠናቀቅ ይወጣ ነበር።

አንጄሊካ የተባለች መስማት የተሳናት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስ የማነበው በፖርቱጋልኛ ነበር፤ ሆኖም ሐሳቡን ለመረዳት በጣም እቸገር ነበር። በብራዚል የምልክት ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ከወጣ ወዲህ ግን ሐሳቡ በደንብ ስለሚገባኝ የታሪኩ ክፍል የሆንኩ ያህል ሆኖ ይሰማኛል!”

የብራዚል የምልክት ቋንቋ ትርጉም ቡድን አባላት ቅጂ ሲያከናውኑ

በ1982 የይሖዋ ምሥክሮች የመጀመሪያውን የምልክት ቋንቋ ጉባኤ በሪዮ ዴ ጄኔሮ አቋቋሙ። በአሁኑ ወቅት በ246 የብራዚል የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች፣ በ337 ቡድኖችና በ63 ቅድመ ቡድኖች ውስጥ የሚያገለግሉ 9,500 ገደማ አስፋፊዎች አሉ።

ይህ መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱ ይሖዋ መስማት የተሳናቸውን ወንድሞችና እህቶች እንደሚወዳቸው ያሳያል። ይህ ውድ ስጦታ ብዙ ሰዎች ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ እንዲማሩና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ እንዲረዳቸው እንጸልያለን።—ዮሐንስ 17:3