ሰኔ 22, 2022
ብራዚል
በብራዚል ሕጋዊ እውቅና ካገኘን ሰባ አምስት ዓመት ሞላን
“እምነታችን፣ ቅንዓታችንና በይሖዋ ላይ ያለን መተማመን ለአፍታም እንኳ ቀንሶ አያውቅም”
ሰኔ 23, 1947 ብራዚል ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ማኅበር (ሶሲዬዳጄ ቶሬ ጄ ቪዢያ ጄ ቢብሊያስ ኤ ትራታዶስ) እውቅና አገኘ። ይህ ሕጋዊ ማኅበር ላለፉት 75 ዓመታት ብራዚል ውስጥ ዋነኛው የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ማኅበር ሆኖ አገልግሏል። ወንድሞቻችን ይህን ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት የሄዱበት መንገድ ግን በብዙ ተቃውሞ የተፈተነ ነበር።
ጥቅምት 13, 1945 የብራዚል አስፋፊዎች የይሖዋ ምሥክሮች በአገሪቱ ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ ድጋፍ የሚጠይቅ ማመልከቻ አሰራጩ። በመላው አገሪቱ፣ 400 ገደማ የሚሆኑ አስፋፊዎች 44,411 ፊርማዎች ማሰባሰብ ችለዋል። ከዚያም ማመልከቻውን ለፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት አስገቡ፤ ሆኖም ምላሽ አላገኙም።
በ1946 ብራዚል አዲስ ሕገ መንግሥት አጸደቀች። ይህ ሕገ መንግሥት፣ ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ የተሰኘው የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ማኅበር በመንግሥት እውቅና እንዲያገኝ የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት አስቀምጦ ነበር። በዚያ ዓመት በየወሩ በአማካይ 442 አስፋፊዎች በአገሪቱ ይሰብኩ እንደነበር ሪፖርት ተደርጓል።
ቀሳውስቱ የይሖዋ ምሥክሮች ባገኙት ሕጋዊ እውቅና ደስተኞች አልነበሩም። ከሦስት ዓመት በኋላ ማለትም ኅዳር 3, 1949 የቀሳውስቱ ጥረት ተሳካ፤ በእነሱ ጫና የብራዚል ፕሬዚዳንት፣ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር እንዲታገድና እንዲዘጋ የሚደነግግ አዋጅ ላይ ፈረሙ። ወንድሞች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰዱት። ይህ የፍርድ ቤት ጉዳይ የተቋጨው ሚያዝያ 8, 1957 አንድ አዲስ ፕሬዚዳንት የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ማኅበር ለገጠመው ችግር እልባት የሚሰጥ ውሳኔ ባሳለፉበት ወቅት ነው።
ወንድሞቻችን በፍርድ ቤት በኩል ያለውን ተፈታታኝ ሁኔታ እየተጋፈጡ ባሉበት ወቅት ይሖዋ በአገሪቱ የሚከናወነውን የስብከት ሥራ መባረኩን ቀጥሎ ነበር። በ1941 የተጠመቀው ወንድም ጅዣልማ ሜንጄስ ሶቶ በብራዚል ያለው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጀመሪያዎቹ አባላት አንዱ ነው፤ እንዲህ ብሏል፦ “እምነታችን፣ ቅንዓታችንና በይሖዋ ላይ ያለን መተማመን ለአፍታም እንኳ ቀንሶ አያውቅም፤ የአስፋፊዎች ቁጥር ጭማሪ ማሳየቱን የቀጠለው ለዚህ ነው። በ1947 ቁጥራችን ለመጀመሪያ ጊዜ 1,000 ሲያልፍ ደስታችን ወደር አልነበረውም።”
ከዚያ ጊዜ ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ብራዚል ውስጥ በአስደናቂ መጠን ጨምሯል። በ2021 ብራዚል ውስጥ 913,479 የሚደርስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ተመዝግቧል፤ በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ደግሞ 2,184,856 ሰዎች ተገኝተዋል። “በእምነት ብርቱ ሁኑ!” የሚል ጭብጥ ያለው የ2021 የክልል ስብሰባ በ15 ቋንቋዎች ተተርጉሟል፤ ከእነዚህ 10 የሚሆኑት አገር በቀል ቋንቋዎች ናቸው።
ይሖዋ በብራዚል የሚከናወነውን ሥራ መባረኩን እንደቀጠለ ማየታችን ያበረታታናል። ወንድሞቻችን የሕግ ተግዳሮቶችን በጽናት አልፈው ለዚህ ደረጃ መብቃታቸው ይሖዋ በእሱ ተስፋ የሚያደርጉትን እንደሚያድን ማረጋገጫ ይሆናል።—ኢሳይያስ 25:9