በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ ለአራት ወራት በቆየው ዘመቻ የተሸፈኑ አካባቢዎችን የሚያሳይ ካርታ። ውስጠኛዎቹ ፎቶግራፎች (ከግራ ወደ ቀኝ)፦ ዋፒሻና፣ ሻቫንቲያ እና ሁንስሪክ ተናጋሪ ወንድሞችና እህቶች በስብከቱ ሥራ ሲካፈሉ

ነሐሴ 8, 2024
ብራዚል

በብራዚል በተካሄደ የስብከት ዘመቻ በ11 ቋንቋዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መዝራት

በብራዚል በተካሄደ የስብከት ዘመቻ በ11 ቋንቋዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መዝራት

ከመጋቢት 1 እስከ ሰኔ 30, 2024 በመላው ብራዚል በተካሄደ የስብከት ዘመቻ ከ1,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ተካፍለዋል። ዘመቻው እንዲካሄድ የተደረገው ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው ጽሑፍ በአገሪቱ በሚነገሩ 11 ቋንቋዎች በወጣበት ሰሞን ነው። በውጤቱም ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

በኖቫ ፔትሮፖሊስ ሁለት እህቶች ሁንስሪክ ተናጋሪ ከሆነ ሰው ጋር ሲወያዩ

በካምፒናፖሊስ የምትኖር ሻቫንቲያ ተናጋሪ የሆነች አንዲት ሴት የይሖዋ ምሥክሮች ሲያነጋግሯት እንዲህ ስትል ጠየቀቻቸው፦ “በቋንቋዬ ቪዲዮ የምታዘጋጁት እናንተ ናችሁ? ለረጅም ጊዜ ሳፈላልጋችሁ ነበር። እንኳን አገኘኋችሁ!” ሴትየዋ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና እንደነበርና ፖርቱጋልኛ መረዳት ባለመቻሏ ምክንያት ጥናቷ እንደተቋረጠ ነገረቻቸው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን በሻቫንቲያ ቋንቋ እየተዘጋጁ መሆኑን ስትገነዘብ የይሖዋ ምሥክሮችን መፈለግ ጀመረች። አሁን ጥናቷን ቀጥላለች።

በሳንታ ማሪዬ ዴ ጄቲባ አንዲት እህት ፖሜራንኛ ከምትናገር ፍላጎት ያሳየች ሴት ጋር ሦስት ጊዜ ረዘም ያለ ውይይት አድርጋ ነበር። በሦስተኛው ውይይታቸው ላይ ሴትየዋ፣ መጀመሪያ ከመገናኘታቸው አንድ ቀን አስቀድማ ወደ አምላክ ጸልያ እንደነበር ለእህታችን ነገረቻት፤ አምላክን በትክክለኛው መንገድ ማምለክ የምትችልበትን መንገድ እንዲያሳያት ጠይቃው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ በደስታ ተቀበለች።

በደቡባዊ ብራዚል በምትገኝ አንዲት አነስተኛ መንደር ውስጥ ወንድሞች የኬይንጋንግ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነች ሴት አነጋገሩ፤ ሴትየዋ ከዚያ በፊት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኝታ አታውቅም። ወንድሞች ለሴትየዋ መዝሙር 83:18⁠ን ካነበቡላት በኋላ የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን አስረዷት። ሴትየዋም በጣም ተደንቃ አምላክ የግል ስም እንዳለው ማንም አስተምሯት እንደማያውቅ ገለጸች። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወዲያውኑ ተስማማች።

ለዘላለም በደስታ ኑር! በሁንስሪክ፣ በማኩሺ፣ በሳቴሬ መዌ፣ በሻቫንቲያ፣ በቲኩና፣ በታሊያን፣ በኔኤንጋቱ፣ በከዋይ፣ በኬይንጋንግ፣ በዋፒሻና እና በፖሜራንኛ፣። ዘመቻው የተካሄደው እነዚህ ጽሑፎች በወጡበት ወቅት ነው

ብዛት ያላቸው ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ ስለሚገኘው “የዘላለም ምሥራች” ይበልጥ እየተማሩ በመሆናቸው በብራዚል ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የተሰማቸውን ደስታ እንጋራለን፤ እነዚህ ሰዎች ከእኛ ጋር ሆነው ለይሖዋ ክብር ይሰጣሉ።—ራእይ 14:6, 7