በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በካብሬኡቫ፣ ብራዚል የተከፈተው አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማዕከል። የውስጠኛው ፎቶግራፍ ከላይ፦ ተማሪዎች የክፍል ውይይት ሲያደርጉ

ታኅሣሥ 20, 2023
ብራዚል

በብራዚል አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማዕከል ተከፈተ

በብራዚል አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማዕከል ተከፈተ

ታኅሣሥ 3, 2023 በካብሬኡቫ፣ ብራዚል አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማዕከል ተወሰነ፤ የውሰና ፕሮግራሙ የተካሄደው በአቅራቢያው ባለ የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ሲሆን የውሰና ንግግሩን ያቀረበው የብራዚል ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኤድዋርዶ ማርቲኔዝ ነበር። ከ2,400 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች በውሰናው ላይ በአካል ተገኝተዋል፤ ከ4,900 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች ደግሞ ፕሮግራሙን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተከታትለዋል።

በስተ ግራ፦ ወንድም ኤድዋርዶ ማርቲኔዝ የውሰና ንግግር ሲያቀርብ። ከላይ በስተ ቀኝ፦ ተሰብሳቢዎች ፕሮግራሙን ሲከታተሉ። ከታች በስተ ቀኝ፦ ለረጅም ጊዜ በአስተማሪነት ያገለገሉ ወንድሞች በፕሮግራሙ ላይ ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው

በዚህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማዕከል ውስጥ በዋነኝነት የሚካሄደው የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት እና ለወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ለሚስቶቻቸው የተዘጋጀው ትምህርት ቤት ነው። ማዕከሉ በአንድ ጊዜ ሦስት ትምህርት ቤቶችንና በየዓመቱ ወደ 600 የሚጠጉ ተማሪዎችን ማስተናገድ ይችላል።

አንድ አስተማሪ፣ ተማሪዎች ተሳትፎ የሚያደርጉበት ውይይት ሲመራ

በ2020 ወንድሞቻችን አንድን ሆቴል ገዝተው ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማዕከልነት ምቹ እንዲሆን አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ጀመሩ። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በሥራው የተካፈሉት ሰዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ 3 የተማሪ ክፍሎች፣ 54 የመኖሪያ ቤቶች፣ አንድ የመመገቢያ ክፍልና ለቢሮዎች የሚሆን ቦታ ያሉትን ይህን ማዕከል ለሥራ ዝግጁ አድርገዋል። ግንባታው ከተጠናቀቀ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የጉብኝት ፕሮግራም ተካሄደ። የዚህ ፕሮግራም ዓላማ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮችና ስለምንሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በደንብ እንዲያውቁ ማድረግ ነበር። የትምህርት ማዕከሉን የጎበኘ አንድ ባለሥልጣን እንዲህ ብሏል፦ “የሠራችሁት ሥራ በጣም የሚያምርና ከፍተኛ ጥራት ያለው ነው። ለአምላክ የምንሠራ ከሆነ፣ ሥራችን መሆን ያለበት እንዲህ ነው።”

በስተ ግራ፦ የአዲሱ የትምህርት ማዕከል የእንግዳ መቆያ ቦታ። በስተ ቀኝ፦ የሕንፃው የተማሪዎች መኖሪያ ቤት

በሥራው የተካፈለ ሮጄሪዮ ብራጋኞሎ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ፕሮጀክቱ በተካሄደበት ጊዜ ሁሉ የይሖዋን አመራር በግልጽ አይተናል። ጥረታችንን የባረከበትን መንገድ ስናይ በመዝሙር 127:1 ላይ የሚገኘው ‘ይሖዋ ቤትን ካልገነባ፣ ግንበኞቹ የሚደክሙት በከንቱ ነው’ የሚለው ሐሳብ እውነት እንደሆነ አስተውለናል።”

ይህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማዕከል በመከፈቱ በጣም ደስተኞች ነን፤ የትምህርት ማዕከሉ በብራዚል ያሉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ‘የማስተማር ጥበባቸውን’ ይበልጥ እንዲያዳብሩ እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።—ቲቶ 1:9