በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የካቲት 4, 2020
ብራዚል

በብራዚል ከደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ በኋላ እየተከናወነ ያለው የጽዳት ሥራ

በብራዚል ከደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ በኋላ እየተከናወነ ያለው የጽዳት ሥራ

ከጥር 18, 2020 አንስቶ ኤስፒሪቶ ሳንቶ እና ሚናስ ዠራይስ በተባሉት የብራዚል ግዛቶች ከፍተኛ ዝናብ በመጣሉ አውዳሚ የሆነ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከስቷል። ጎርፉ ቤቶችን አፍርሷል፣ መኪኖችን ጠራርጎ ወስዷል እንዲሁም ዛፎችን ነቃቅሏል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው እንደተፈናቀሉና ከ60 የሚበልጡ ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል።

ኤስፒሪቶ ሳንቶ

ኢኮንያ እና አልፍሬዶ ሻቬስ በተባሉት አካባቢዎች የደረሰው ጎርፍ የ27 ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መኖሪያ በሆኑ ዘጠኝ ቤቶች ላይ ጉዳት አስከትሏል። ደስ የሚለው ከወንድሞቻችን መካከል ሕይወቱ ያለፈም ሆነ የአካል ጉዳት የደረሰበት የለም።

በአካባቢው የሚኖሩ 100 ገደማ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በጎርፉ የተጎዱ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል። ወንድሞች በሽማግሌዎች አመራር ሥር ሆነው ምግብ፣ ውኃና አልባሳት መዋጮ አድርገዋል። በተጨማሪም በወንድሞቻችንም ሆነ የይሖዋ ምሥክር ባልሆኑ ጎረቤቶቻቸው ቤት ውስጥ የገባውን ጭቃ በመጥረግና ቤቶቻቸውን በማጽዳት እገዛ አበርክተዋል።

ሚናስ ዠራይስ

ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን መካከል ሕይወቱ ያለፈም ሆነ የአካል ጉዳት የደረሰበት የለም። ሆኖም በአምስት የስብሰባ አዳራሾች ላይ ጉዳት ደርሷል፤ እንዲሁም 50 ገደማ የሚሆኑ ቤተሰቦች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። አንዳንድ ወንድሞች ጎርፉ ወደ ላይ ከፍ እያለ በመምጣቱ የተነሳ ከቤታቸው መውጣት አልቻሉም ነበር፤ በመሆኑም ከሁለተኛ ፎቅ ላይ በጀልባ መወሰድ አስፈልጓቸዋል። ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ በእምነት ባልንጀሮቻቸው ቤት ውስጥ ተጠልለዋል።

በኤስፒሪቶ ሳንቶ እና በሚናስ ዠራይስ የእርዳታ ሥራውን ለማስተባበር የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል። የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ ጉዳት ለደረሰባቸው አስፋፊዎች ቁሳዊና መንፈሳዊ እርዳታ ለማቅረብ ሲሉ ከወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ከአካባቢው ሽማግሌዎች ጋር ተባብረው እየሠሩ ነው።

በጎርፉ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወንድሞቻችን መጸለያችንን እንቀጥላለን። ይሖዋ በክርስቲያን የወንድማማች ማኅበራችን አማካኝነት ለወንድሞቻችን ማበረታቻ፣ ማጽናኛና እርዳታ እየሰጣቸው በመሆኑ አመስጋኞች ነን።—መዝሙር 28:7