ጥር 27, 2021
ብራዚል
በብራዚል የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች እምብዛም ባልተሰበከባቸው አካባቢዎች ሰበኩ
ብራዚል ውስጥ ጉባኤ የሌለባቸው 1,500 ገደማ ከተሞች አሉ። ከእነዚህ ከተሞች አንዳንዶቹ በጣም ርቀው የሚገኙ በመሆናቸው ብዙዎቹ ነዋሪዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ጨርሶ ተገናኝተው አያውቁም። በዚህም ምክንያት የብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ 2020 በእነዚህ ከተሞች ለመስበክ ልዩ ዘመቻ አዘጋጀ። ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በተጣሉት ገደቦች የተነሳ ዘመቻው የተካሄደው በደብዳቤ አማካኝነት ነው። በ3,000 ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ አስፋፊዎች በዘመቻው ተካፍለዋል።
አስፋፊዎቹ ስለተመደበላቸው ከተማ ኢንተርኔት ላይ ምርምር ካደረጉ በኋላ የከተማው ነዋሪዎች የሚያሳስባቸውን ነገር ግምት ውስጥ በማስገባት ደብዳቤዎቻቸውን ጻፉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት አቅኚ በቶካንቺንስ ግዛት በምትገኝ ከተማ ለሚኖሩ ሰዎች ደብዳቤዎች ጽፋ ነበር። ይህች አቅኚ በአካባቢው ሰደድ እሳት ተነስቶ አጋጥሞ እንደነበረ አወቀች። በመሆኑም በደብዳቤዋ ላይ ከራእይ 21:5 የተወሰደ ሐሳብ ከጠቀሰች በኋላ ይሖዋ ወደፊት ‘ሁሉንም ነገር አዲስ እንደሚያደርግ’ እና በምድር ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት እንደሚያስተካክል ገለጸች። ከጥቂት ቀናት በኋላ አንዲት ሴት ለአቅኚዋ የድምፅ መልእክት ላከችላት፤ ሴትየዋ አምላክ “የተሻለ ለውጥ እንደሚያመጣ” የሚገልጽ ሐሳብ በማንበቧ በጣም እንደተደሰተች ገለጸችላት። ከዚያም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥያቄ አቀረበች።
አንዲት ሴት፣ ለአንዲት እህት የላከችው የጽሑፍ መልእክት የዘመቻውን ውጤታማነት በሚገባ ያሳያል። መልእክቱ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ በአንቺ ተጠቅሞ መልእክት እንደላከልኝ ተሰምቶኛል። . . . አመሰግንሻለሁ! አምላክ እንደሚወደኝ ብሎም እኔንና ቤተሰቤን እንደሚንከባከበን እንደገና እንዳምን አድርገሽኛል! እንደምወደድ ተሰምቶኛል። ባላውቅሽም እንኳ የጸሎቴ መልስ ነሽ! ከልቤ አመሰግንሻለሁ!”
በፔርቶፖሊስ፣ ሪዮ ዴ ጄኔሮ በሚገኘው በኢታማራቲ ጉባኤ የሚያገለግል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ በዘመቻው የተካፈሉ ወንድሞችና እህቶች ምን እንደተሰማቸው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ገለልተኛ ክልል ሄደው እንዳገለገሉ ልዩ አቅኚዎች እንደሆንን ተሰምቶናል። ብዙዎቹ ወንድሞችና እህቶች፣ ባሉበት ሁኔታ እንዲሁም በቤተሰብ ኃላፊነታቸው የተነሳ በዚህ ዓይነት ዘመቻ የመካፈል አጋጣሚ ብዙ ጊዜ አያገኙም።”
ይሖዋ ይህንን ዘመቻ እንደባረከው በግልጽ ማየት ይቻላል። ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” እንዲሰበክ አስተዋጽኦ የማድረግ መብት በማግኘታችን አመስጋኞች ነን።—ቆላስይስ 1:23