በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 10, 2019
ብራዚል

በብራዚል ገጠራማ አካባቢዎች የተደረገ ልዩ የስብከት ዘመቻ

በብራዚል ገጠራማ አካባቢዎች የተደረገ ልዩ የስብከት ዘመቻ

በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በብራዚል ገጠራማ አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመስበክ ልዩ ጥረት እያደረጉ ነው። ይህ ልዩ የስብከት ዘመቻ የጀመረው መስከረም 1, 2018 ሲሆን እስከ ታኅሣሥ 31, 2019 ድረስ ይቀጥላል። እስከ አሁን ድረስ ከ80,000 በላይ አስፋፊዎች በዘመቻው ተካፍለዋል፤ ከ16,000 የሚበልጡ ሰዎችንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀምረዋል።

ብራዚል ከዓለማችን አምስተኛዋ ትልቅ አገር ናት። ብራዚል ውስጥ 28 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች በገጠራማ አካባቢዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። ሌሎች 22 ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች ደግሞ ርቀው በሚገኙ መንደሮችና ሰፈሮች ውስጥ ይኖራሉ። በልዩ ዘመቻው ከ1,600 በላይ ክልሎችን መሸፈን ተችሏል። በዘመቻው የተካፈሉ አንዳንድ አስፋፊዎች ሰዎችን ለማግኘት ከ2,000 ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ አስፈልጓቸዋል።

አንድ አስፋፊ ወደ አንድ ቤት ሲሄድ አረጋዊ የሆኑ አንድ ሰውዬ ከእርሻ የሰበሰቡትን ቡና እየፈለፈሉ አገኛቸው። እኚህ ሰው አስፋፊውን ወደ ቤት እንዲገባ ጋበዙትና ባለቤታቸውን ጠርተው “የመጣው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሊነግረን ስለሆነ እንስማው!” አሏት።

ሰውየውና ባለቤታቸው አስፋፊውን ብዙ ጥያቄዎች ይጠይቁት ጀመር። ሙታን ስላሉበት ሁኔታ፣ አምላክ መከራ እንዲደርስብን የፈቀደው ለምን እንደሆነ፣ አስራት መክፈል ይኖርባቸው እንደሆነና እንዳልሆነ፣ በቤተሰብ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ስለሚቻልበት መንገድና ስለ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ጠየቁት። ሰውየው አስፋፊው መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅሞ በሰጣቸው መልስ ተገርመው ጠዋት ላይ ጸልየው እንደነበረና ጥያቄዎቻቸው መልስ ያገኙ እንደሆነ አምላክን እንደጠየቁት ለወንድም ነገሩት። ሰውየውና ቤተሰባቸው በዚያው ምሽት ለመጀመሪያ ጊዜ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኙ፤ በአሁኑ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸውን ቀጥለዋል።

በሌላ አካባቢ ደግሞ አስፋፊዎች ከቤት ወደ ቤት እያገለገሉ ሳሉ ከባድ ዝናብ በመጣሉ ወደ አንድ ጤና ጣቢያ ሄደው ለመጠለል ተገደዱ። እዚያ ያገኟትን አንዲት እናትና ሴት ልጇን፣ አምላክን ምን መጠየቅ እንደሚፈልጉ ጠየቋቸው። ልጅቷም በሞት የተለየቻትን አያቷን ዳግመኛ ማግኘት እንደምትፈልግ ነገረቻቸው። አስፋፊዎቹ ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚናገሩ ጥቅሶችን ካነበቡላቸው በኋላ ትንሣኤ በቅርቡ እውን ይሆናል! የሚለውን ቪዲዮ አሳዩአቸው።

ከጊዜ በኋላ አስፋፊዎቹ ወደ ሴትየዋ ቤት ሄደው ከእሷና ከቤተሰቧ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመሩ። ሴትየዋና ሴት ልጆቿ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ከተማ በሚደረግ ስብሰባ ላይ የተገኙ ከመሆኑም ሌላ በስልክ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸውን ቀጥለዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” ተገዢዎች እንደሚኖሩት አስቀድሞ ተናግሯል። በብራዚል ገጠራማ አካባቢዎች እየተደረገ ያለው ልዩ ዘመቻ ይሖዋ ይህ ትንቢት ሲፈጸም ማየት እንደሚፈልግ የሚያረጋግጥ ነው።—መዝሙር 72:8