በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሰኔ 25, 2020
ብራዚል

በአማዞን የሚገኙ ወንድሞቻችን እርዳታ ተደረገላቸው

በአማዞን የሚገኙ ወንድሞቻችን እርዳታ ተደረገላቸው

የብራዚል ቅርንጫፍ ኮሚቴ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለኢኮኖሚ ችግር የተዳረጉ አስፋፊዎችን ለመርዳት 18 የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። ኮሚቴዎቹ በመላው አገሪቱ ለሚገኙ 12,000 ገደማ ጉባኤዎች ድጋፍ እያደረጉ ነው፤ ከእነዚህ መካከል በአማዞን ወንዝ ዙሪያ የሚኖሩ ርቀው የሚገኙ ወንድሞቻችን ይገኙበታል። እስካሁን ድረስ በአማዞን የሚኖሩ 131 ቤተሰቦች እርዳታ ተደርጎላቸዋል።

የአማዞናስ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በማናውስ ያለው የእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ አንድ ቤተሰብ ለአንድ ወር የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች የያዙ ጥቅሎች አዘጋጅቷል። ጥቅሎቹ እንደ ባቄላ፣ የካሳቫ ዱቄት፣ ሩዝና የዱቄት ወተት ያሉ የምግብ ዓይነቶችን እንዲሁም እንደ ሳሙና፣ ሶፍት፣ የጥርስ ብሩሽና የጥርስ ሳሙና ያሉ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን የያዙ ናቸው። ወንድሞች ጥቅሎቹን በአቅራቢያቸው ወዳለው የማናካፑሩ ወደብ ከላኩ በኋላ ሜምቤካንና ላጎ ዶ ካስታኖን ጨምሮ ርቀው ወደሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በጀልባ አከፋፍለዋል።

በላጎ ዶ ካስታኖ የምትኖር ማሪኔልማ የተባለች እህት የምግብ እርዳታ ከተደረገላት በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “ከሁሉ አስቀድሜ ይሖዋን ላመሰግነው እፈልጋለሁ፤ ይሖዋ ተንከባክቦናል። እዚህ ያለነው ሰዎች ምግብ መግዛት የምንችልበት ምንም መንገድ ስላልነበረ እርዳታ በእጅጉ ያስፈልገን ነበር። በተጨማሪም ላሳዩን ልግስናና ፍቅር ወንድሞችን እናመሰግናለን። የስድስት ዓመት ልጄ የተሰጠንን እርዳታ እያወጣሁ ሳስቀምጥ እያየኝ ስለነበር አጋጣሚውን ተጠቅሜ ይሖዋ በወንድሞቻችን በኩል እንዴት እየረዳን እንዳለ ነገርኩት። ከዚያም ትንሹ ልጄ ‘እማ፣ ታዲያ ለምን ይሖዋን አናመሰግነውም?’ አለኝ።”

ከቤተሰቡ ጋር በካፒራንጋ ከተማ የሚኖረው ወንድም ጆናስ ሞንቴሮ ለእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴው ደብዳቤ ጽፎ ነበር፤ ደብዳቤው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “ላደረጋችሁልን እርዳታ በጣም እናመሰግናለን። በእናንተ በኩል የይሖዋን ፍቅር ማየት ችለናል። የዚህ ዓለም አቀፍ ቤተሰብ አባል መሆን በእርግጥም ትልቅ መብት ነው።”

በእርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግሉት ወንድሞችም በዚህ ዝግጅት በመካፈላቸው ተጠቅመዋል። በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግል አይዛክ ኢማኑዌል ራማሎ ዴ ኦሊቬራ የሚባል የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “በአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ ሳገለግል በየዕለቱ እምነቴ እየተጠናከረ እንዳለ ይሰማኛል። እርዳታ ከሚደረግላቸው ወንድሞች በላይ እየተጠቀምኩ ያለሁት እኔ እንደሆንኩ እርግጠኛ ነኝ።”

ይህ ወረርሽኝ በተከሰተበት በዚህ ወቅት ይሖዋ አገልጋዮቹ የትም ይሁኑ የት እንደሚንከባከባቸው ማየታችን እምነታችንን ያጠናክረዋል።—መዝሙር 94:14