በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በስተ ግራ፦ ከሳኦ ፓውሎ አቅራቢያ የሚገኘው የብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ። በስተ ቀኝ፦ በብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ እድሳት ላይ እንዲሳተፉ የተመደቡ ፈቃደኛ ሠራተኞች

ግንቦት 6, 2022
ብራዚል

የብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ እድሳት ተጀመረ

የብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ እድሳት ተጀመረ

በብራዚል ቅርንጫፍ ቢሮ መጠነ ሰፊ የእድሳት ሥራ መካሄድ ጀምሯል፤ ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኘው ከሳኦ ፓውሎ ከተማ በስተ ምዕራብ 140 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። የእድሳቱ ዓላማ የቤቴል ሕንፃዎቹን ማደስና የግንባታ ቁሳቁሶቹን ማሻሻል ነው። አገልግሎት እየሰጠ ያለን የቤቴል ሕንፃ ማደስ ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት። የእድሳት ሥራው የቅርንጫፍ ቢሮውን እንቅስቃሴ በማያስተጓጉል መልኩ መካሄድ አለበት። ለምሳሌ ቤቴላውያኑ ክፍላቸው በሚታደስበት ወቅት ጊዜያዊ መኖሪያ ውስጥ መቆየት ያስፈልጋቸዋል። ፕሮጀክቱ በአምስት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

ወንድሞች ሁሉንም ቢሮዎችና ያሉትን 650 የመኖሪያ ክፍሎች ጨምሮ 75,000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው አካባቢ ማደስ ይጠበቅባቸዋል። ማሻሻያው የቅርንጫፍ ቢሮው ሕንፃዎች ለተለያዩ ዓላማዎች እንዲውሉና ይበልጥ ውጤታማ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል። ለምሳሌ ቢሮዎቹ ተነቃቃይ ግድግዳዎች ይኖሯቸዋል፤ ይህም ቦታውን እንደ አስፈላጊነቱ በፍጥነት በመቀያየር ለተለያየ አገልግሎት ለማዋል ያስችላል። እያንዳንዱ መኖሪያ ክፍል አነስተኛ ኩሽናና ልብስ ማጠቢያ ቦታ ይኖረዋል። በተጨማሪም የቅርንጫፍ ቢሮውን የውኃና የኃይል ፍጆታ ለመቀነስ ሲባል ሥነ ምኅዳሩን የማይጎዱ ዘመናዊ መሣሪያዎች ይገጠማሉ።

በፕሮጀክቱ ላይ የሚካፈሉት ወንድሞችና እህቶች በቅርንጫፍ ቢሮው ግቢ ውስጥ ጊዜያዊ ቤት ይኖራቸዋል። ቀደም ሲል መጋዘን የነበረ አንድ ሕንፃ ተስተካክሎ 25 መኖሪያ ክፍሎች እንዲይዝ ተደርጓል። በተጨማሪም 91 ኮንቴነሮች ወደ ጊዜያዊ መኖሪያነት ተቀይረው ከቤቴል ሕንፃው አጠገብ ባለው የቤቴል እርሻ ላይ ተቀምጠዋል።

ለፈቃደኛ ሠራተኞች ጊዜያዊ መኖሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ኮንቴነሮች

በፕሮጀክቱ የሚካፈለው ወንድም ጆኤል ግሪጎር እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ድርጅት ሥራውን እያከናወነ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡንም እያሠለጠነ ነው። አብዛኞቹ ፈቃደኛ ሠራተኞች ጨርሶ የግንባታ ሙያ አልነበራቸውም ሊባል ይችላል፤ አሁን ግን ብዙ ሥልጠና ስላገኙ እነሱም ሌሎችን ማሠልጠን ጀምረዋል።”

ይሖዋ ሕዝቦቹ በዚህና በሌሎች ቲኦክራሲያዊ ፕሮጀክቶች ለመካፈል ‘ራሳቸውን በፈቃደኝነት ሲያቀርቡ’ አትረፍርፎ አንደሚባርካቸው እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 110:3