መስከረም 19, 2023
ቦሊቪያ
በቦሊቪያ በቀረበ ዓለም አቀፍ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ ለአእምሮ ጤና ጉዳይ ትኩረት ተሰጠ
ከግንቦት 31 እስከ ሰኔ 11, 2023 ቦሊቪያ ውስጥ በሳንታ ክሩዝ ዴ ላ ሲዬራ፣ የሳንታ ክሩዝ ዓለም አቀፍ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ተካሂዷል። አውደ ርዕዩን ከ120,000 የሚበልጡ ሰዎች ጎብኝተውታል። ለወንድሞች በተመደበው ቦታ ላይ “የአእምሮ ጤንነት—መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው እርዳታ” የሚል ርዕስ ያለው መጠበቂያ ግንብ ቁጥር 1 2023 በጉልህ ይታይ ነበር።
በአውደ ርዕዩ ላይ ወደ 200 የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች ለይሖዋ ምሥክሮች በተመደበው ቦታ ላይ የሠሩ ሲሆን ከ20,000 የሚበልጡ ጎብኚዎችን አነጋግረዋል። ከድረ ገጻችን ላይ የተወሰዱ ቪዲዮዎች በቴሌቪዥን ቀርበዋል፤ እንዲሁም ጎብኚዎች jw.orgን በመጠቀም በተለያዩ ርዕሶች ላይ ምርምር ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ተጠቁመዋል። ወደ 5,500 የሚሆኑ ጽሑፎች ተበርክተዋል፤ እንዲሁም 600 ገደማ ቪዲዮዎች ታይተዋል። በተጨማሪም ለይሖዋ ምሥክሮች የተመደበውን ክፍል የጎበኙ 45 ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲመራላቸው በjw.org አማካኝነት ጠይቀዋል።
የአእምሮ ጤና የሚለውን ርዕስ የተመለከተች አንዲት ሴት ወደ አንዲት እህት ቀርባ እናቷ የአእምሮና ጤና እና የስሜት መቃወስ ችግር እንዳለባት ገለጸችላት። እሷ ራሷም በጣም እንደምትጨነቅና ድባቴ እንደሚያስቸግራት ነገረቻት። እህትም ስለ አእምሮ ጤና የሚናገረውን መጠበቂያ ግንብ መጽሔት እና ለዘላለም በደስታ ኑር! ብሮሹር ስልኳ ላይ እንድታወርድት ረዳቻት። ሴትየዋም በjw.org ላይ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጠየቂያ ቅጽ ወዲያውኑ ሞላች።
በአውደ ርዕዩ ላይ ስለ አእምሮ ጤና የሚናገረውን መጠበቂያ ግንብ የወሰደ አንድ የሥነ ልቦና ባለሙያ እንዲህ በማለት አስተያየት ሰጥቷል፦ “በዚህ ጽሑፍ ላይ ያለውን ሐሳብ ለታካሚዎቼ ለማካፈል አስቤያለሁ። በጽሑፉ ላይ የሰፈረው መረጃና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶቹ እንደሚጠቅሟቸው እርግጠኛ ነኝ።” እናቷን በቅርቡ በሞት ያጣች ሌላ ሴት ደግሞ jw.org ላይ “ሰላም እና ደስታ” በሚለው ዓምድ ሥር “ወላጅ ሲሞት” የሚለውን ርዕስ ስትመለከት ተበረታታለች።
በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የአእምሮ ጤና ችግርና የስሜት መቃወስ ያጋጥማቸዋል፤ በቦሊቪያ የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚሰጠውን ተግባራዊ ምክርና ማጽናኛ እንዲያገኙ ሰዎችን በመርዳታቸው ተደስተዋል።—መዝሙር 34:18