በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 17, 2021
ቦሊቪያ

አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በኬችዋ (ቦሊቪያ) ቋንቋ ወጣ

አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በኬችዋ (ቦሊቪያ) ቋንቋ ወጣ

ጥቅምት 24, 2021 የቦሊቪያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዳግላስ ሊትል አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በኬችዋ (ቦሊቪያ) ቋንቋ መውጣቱን አበሰረ። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በኤሌክትሮኒክ ቅጂ መውጣቱ የተነገረው አስቀድሞ በተቀዳ ንግግር አማካኝነት ሲሆን ፕሮግራሙ በቦሊቪያ ከ4,000 ለሚበልጡ ተመልካቾች በቀጥታ ተላልፏል። ከሚያዝያ 2022 አንስቶ የታተሙ ቅጂዎችን ማግኘት እንደሚቻል ይጠበቃል።

ኬችዋ (ቦሊቪያ) የተለያዩ ቀበሌኛዎች ያሉት ቋንቋ ነው፤ አንዳንድ ቃላት በተለያዩ ክልሎች የተለያየ ትርጉም ሊኖራቸው ይችላል። ለዚህም ሲባል በአዲሱ ዓለም ትርጉም ላይ ብዙ የግርጌ ማስታወሻዎች እንዲካተቱ ተደርጓል፤ እነዚህ የግርጌ ማስታወሻዎች አንዳንድ ቃላት በተለያዩ ቀበሌኛዎች ያላቸውን የተለያየ ትርጉም ያብራራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ በኬችዋ (ቦሊቪያ) ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተረጎመው በ1880 ነው። ሆኖም በአብዛኞቹ ትርጉሞች ላይ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም የሚገኘው በግርጌ ማስታወሻዎች ላይ ብቻ ነው፤ ወይም ደግሞ “እግዚአብሔር” በሚለው የማዕረግ ስም ተተክቷል። አንድ ተርጓሚ “የአምላክ ስም ያለበት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በማግኘታችን በጣም ተደስተናል” ብሏል።

የትርጉም ሥራው ይከናወን በነበረበት ወቅት ብዙዎቹ ተርጓሚዎች የተለያዩ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል፤ ለምሳሌ፣ የታመሙ የቤተሰባቸውን አባላት ማስታመም ያስፈለጋቸው ነበሩ። በተጨማሪም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የፈጠረው ሁኔታም ለፕሮጀክቱ እንቅፋት የሚፈጥር ነበር። አንድ ተርጓሚ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥቷል፦ “ሥራው ሊጠናቀቅና ከተጠበቀው ቀን አስቀድሞ መጽሐፍ ቅዱሱ ሊወጣ የቻለው በይሖዋ እርዳታ ነው።”

በኬችዋ (ቦሊቪያ) ቋንቋ የወጣው አዲስ ዓለም ትርጉም የቋንቋው ተናጋሪዎች “እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ይረዳል የሚል እምነት አለን።—1 ጢሞቴዎስ 2:4