በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 1, 2021
ቦሊቪያ

አዲስ ዓለም ትርጉም በአይማራ ቋንቋ ወጣ

አዲስ ዓለም ትርጉም በአይማራ ቋንቋ ወጣ

ሰኔ 27, 2021 አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በአይማራ ቋንቋ በዲጂታል ፎርማት ወጣ። አስቀድሞ የተቀረጸው ፕሮግራም በቦሊቪያ ለሚገኙ ጉባኤዎችና ቡድኖች ሁሉ ተላልፏል። መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱን ያበሰረው የቦሊቪያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኔልቮ ካቫሊዬሪ ነው።

አጭር መረጃ

  • የአይማራ ተናጋሪ የሆኑት ከ1.6 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በዋነኝነት የሚኖሩት በአንዲስ ተራሮች በሚገኘው በቲቲካካ ሐይቅ አካባቢ ነው

  • ቦሊቪያ ውስጥ በቀደምት የአገሬው ተወላጆች ከሚነገሩት 36 ቋንቋዎች መካከል በተናጋሪዎች ብዛት ሁለተኛውን ደረጃ የሚይዘው አይማራ ነው

  • የአይማራ ቋንቋን በሚጠቀሙ በብራዚል፣ በቦሊቪያ፣ በቺሊ፣ በአርጀንቲና እና በፔሩ በሚገኙ ከ60 በላይ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 2,000 ገደማ አስፋፊዎች አሉ

  • በሥራው የተካፈሉት 6 ተርጓሚዎች ሥራውን ለማጠናቀቅ 4 ዓመት ፈጅቶባቸዋል

አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ለአይማራ ተናጋሪዎች የሰጣቸው ግሩም ስጦታ ነው። አሁን መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ በሚያውቁትና በሚረዱት ቋንቋ ማንበብ ይችላሉ። ይሖዋ በቀጥታ እያነጋገራቸው እንዳለ ሆኖ ይሰማቸዋል።”

የቦሊቪያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ማውሪስዮ ሀንደል እንዲህ ብሏል፦ “የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአይማራ ቋንቋ በ2017 ከወጣ ጊዜ አንስቶ ብዙዎች ይህ ትርጉም ልባቸውን እንደነካው በመናገር አድናቆታቸውን ገልጸዋል። አሁን ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አግኝተናል፤ ትርጉሙ የቋንቋውን ተፈጥሯዊ ለዛ የጠበቀና ግልጽ ነው። ይህ ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ የዚህ መጽሐፍ ባለቤት ወደሆነው ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ እንደሚረዳ እርግጠኞች ነን።”

ይህ መጽሐፍ ቅዱስ አይማራ ተናጋሪ የሆኑ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የመዝሙራዊውን ሐሳብ በማስተጋባት “ማዳንህን እናፍቃለሁ፤ ቃልህ ተስፋዬ ነውና” እንዲሉ እንደሚያነሳሳቸው እንተማመናለን።—መዝሙር 119:81