በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የቦትስዋና ወንድሞችና እህቶች በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ሲካፈሉ

የካቲት 19, 2024
ቦትስዋና

በቦትስዋና ሃይማኖታዊ ነፃነት ካገኘን 50 ዓመት አስቆጠርን

በቦትስዋና ሃይማኖታዊ ነፃነት ካገኘን 50 ዓመት አስቆጠርን

የካቲት 20, 2024 በቦትስዋና የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ያገኙበት 50ኛ ዓመት ነው። የቦትስዋና ወንድሞቻችን በ1974 ሕጋዊ እውቅና ከማግኘታቸው በፊት በተለያዩ ጊዜያት ገደቦች ተጥለውባቸው ነበር፤ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴያቸው ሙሉ በሙሉ የታገደበት ጊዜም ነበር።

በወረዳ ስብሰባ ላይ ወንድሞችና እህቶች ፎቶግራፍ ሲነሱ፣ 1965፣ ማሃላፕዬ፣ ቦትስዋና

የመንግሥቱ እውነት ያን ጊዜ ቤቹዋናላንድ ተብላ ወደምትጠራው ቦትስዋና የደረሰው በ1929 ነው። ይሁንና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያት የተከሰተውን የፖለቲካ ነውጥ ተከትሎ መንግሥት በሥራችንና በምናሰራጫቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ላይ ገደቦች ጣለ። በ1959 እነዚህ ገደቦች ሲነሱ የይሖዋ ምሥክሮች የተገኘውን አንጻራዊ ነፃነት በመጠቀም መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ቀጠሉ።

በ1972 ቦትስዋና ውስጥ ሁሉም ድርጅቶች በመንግሥት እንዲመዘገቡ የሚደነግግ ሕግ ጸደቀ። ወንድሞቻችን ይህን ለማድረግ ሲሞክሩ ግን ማመልከቻቸው ውድቅ ሆነ፤ በ20 ቀናት ውስጥ ሁሉንም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን እንዲያቆሙ ታዘዙ። ቦትስዋና ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች እገዳ ውስጥ ገቡ። በአገልግሎት ወይም በጉባኤ ስብሰባ ሲሳተፍ የተገኘ ሰው የሰባት ዓመት እስር ይፈረድበት ነበር። ያም ሆኖ ወንድሞቻችን በድብቅ መሰብሰባቸውን ቀጠሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ጫካ ውስጥ ሰው በማይደርስባቸው አካባቢዎች ስብሰባዎች የሚደረጉበት ጊዜ ነበር። ወንድም ቶሚ ማሩፒንግ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ እንዲህ ብሏል፦ “እገዳ ሥር የነበርን ቢሆንም መስበካችንን እና መሰብሰባችንን ለመቀጠል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጠን ነበር። ይሖዋ መቼም ከእኛ እንደማይለይ እርግጠኞች ነበርን፤ ደግሞም አላሳፈረንም።”

“በትዕግሥት ጠብቁ”! በተሰኘው የ2023 የክልል ስብሰባ ላይ የተገኙ ተሰብሳቢዎች፣ ጋቦሮኔ፣ ቦትስዋና

የካቲት 20, 1974 መንግሥት የቀድሞውን ውሳኔ በመቀልበስ የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ ፈቀደላቸው። በአሁኑ ወቅት ቦትስዋና ውስጥ በ42 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 2,400 ገደማ አስፋፊዎች አሉ። ስብሰባዎች በሴጽዋና፣ በሾና፣ በቦትስዋና ምልክት ቋንቋ፣ በእንግሊዝኛ እና በካላንጋ (ቦትስዋና) ቋንቋዎች ይካሄዳሉ። እገዳው ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ በቦትስዋና ሚስዮናዊ ሆኖ ማገልገል የጀመረው ወንድም ሂዩ ኮርሚካን እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞቻችንና እህቶች በመንፈሳዊ ማደጋቸውን ቀጥለዋል። በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ አብረን የመሰብሰብ ነፃነት ያለን መሆኑ በይሖዋ ሕዝብ መካከል ያለውን እውነተኛ አንድነት ለማጣጣም አስችሎናል።”

የቦትስዋና ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጽናት አሁንም እንደሚያረጋግጠው ይሖዋ ‘ትእዛዛቱን ለመጠበቅ’ የሚተጉ ታማኝ አገልጋዮቹን ሁልጊዜም ይባርካል።​—1 ዮሐንስ 5:3