በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 5, 2021
ቬኔዙዌላ

በቬኔዙዌላ ምልክት ቋንቋ የወጡት የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት

በቬኔዙዌላ ምልክት ቋንቋ የወጡት የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት

ጥቅምት 30, 2021 የማቴዎስና የዮሐንስ መጻሕፍት በቬኔዙዌላ ምልክት ቋንቋ ወጡ። ከ2,200 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች አስቀድሞ የተቀዳውን ልዩ ፕሮግራም በቀጥታ ተከታትለዋል። የቬኔዙዌላ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ሚጌል ጊዬን መጻሕፍቱ መውጣታቸውን አብስሯል። ቅርንጫፍ ቢሮው ከ2006 አንስቶ 7,000 የሚጠጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቬኔዙዌላ ምልክት ቋንቋ ተርጉሟል፤ ሆኖም ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በዚህ የምልክት ቋንቋ የተዘጋጀው አሁን ነው።

የርቀት የትርጉም ቢሮ ውስጥ

ተርጓሚዎቹ ሥራቸውን የጀመሩት በማቴዎስና በዮሐንስ ወንጌሎች ነው። ምክንያቱም የኢየሱስን ሕይወት የሚተርኩት እነዚህ መጻሕፍት በስፋት ይታወቃሉ፤ ደግሞም በትረካ መልክ መዘጋጀታቸው ከሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ይልቅ ለመተርጎም ቀላል ያደርጋቸዋል።

በ2003 በምዕራብ ቬኔዙዌላ በምትገኘው የካቢማስ ከተማ የመጀመሪያው የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ተቋቋመ። በአሁኑ ወቅት፣ በመላ አገሪቱ በ53 የምልክት ቋንቋ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 1,204 አስፋፊዎች አሉ። በቬኔዙዌላ የሚኖሩ በርካታ መስማት የተሳናቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የመማር ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፤ ሆኖም የስፓንኛ ምልክት ቋንቋ እነሱ ከሚጠቀሙበት ምልክት ቋንቋ በጣም ስለሚለይ ሁኔታውን አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል።

አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አንድ መስማት የተሳነው ሰው በስፓንኛ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ አገኘ፤ ሲያነበው ግን ምንም ሊገባው አልቻለም። አምላክ እንዲረዳው ጸለየ። . . . ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን በቬኔዙዌላ ምልክት ቋንቋ መማር እንደሚችል ተነገረው፤ እሱም ወዲያውኑ ለማጥናት ተስማማ።”

ስድስት ተርጓሚዎችን ያቀፈው የትርጉም ቡድን መጻሕፍቱን ለመተርጎም አሥር ወር ፈጅቶበታል። ከአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የመጡ ሰባት መስማት የተሳናቸው ወንድሞች ሥራውን እንዲገመግሙ ተደርጓል። ይህም ተርጓሚዎቹ በክልሎቹ መካከል ያለውን የቋንቋ ልዩነት ያገናዘበ ትርጉም ማዘጋጀት እንዲችሉ ረድቷቸዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ ተርጓሚዎቹ በተለያዩ ቦታዎች ሆነው በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ለመሥራት ተገድደዋል። ሥራቸውን ይበልጥ ተፈታታኝ ያደረገባቸው ጥሩ ኢንተርኔት አለመኖሩ ነው። አንድ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታው ቀላል አልነበረም፤ ይሖዋ ግን ማንኛውንም እንቅፋት እንድንወጣ ረድቶናል።”

በቬኔዙዌላ ያሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በሙሉ በቋንቋቸው ከተዘጋጀውና “እንደተጣራ ብር” ከሆነው የይሖዋ ቃል የተሟላ ጥቅም እንዲያገኙ ጸሎታችን ነው።—መዝሙር 12:6