በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቬኔዙዌላ ያሉ ወንድሞችና እህቶች የመታሰቢያውን በዓል ሲያከብሩ

ሚያዝያ 21, 2021
ቬኔዙዌላ

የ2021 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—ቬኔዙዌላ

በቬኔዙዌላ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም የመታሰቢያውን በዓል ማክበርና ሌሎችን መጋበዝ ችለዋል

የ2021 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—ቬኔዙዌላ

በቬኔዙዌላ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የኢኮኖሚ ችግርንና አለመረጋጋትን እንዲሁም የኮቪድ-19⁠ን ወረርሽኝ ጨምሮ በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ ነው። ያም ሆኖ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ማክበርና ሌሎችን መጋበዝ ችለዋል።

ለምሳሌ ያህል፣ በኮሎምቢያ ድንበር አቅራቢያ በአፑሬ ግዛት በምትገኝ ላ ቪክቶሪያ የተባለች ከተማ የመታሰቢያው በዓል ከመከበሩ ከሁለት ሳምንት በፊት ከባድ ጦርነት ተከፈተ። በአካባቢው በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ ያሉት አስፋፊዎች በሙሉ ወደ ኮሎምቢያ ለመሸሽ ተገደዱ። የቬኔዙዌላ ወንድሞች፣ በኮሎምቢያ አሮኩዊታ ጉባኤ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ባደረጉላቸው እርዳታ የመታሰቢያውን በዓል በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት መከታተል ችለዋል።

አንድ ባልና ሚስት በመልእክት መቀበያ ሬዲዮ አማካኝነት የመታሰቢያውን በዓል ንግግር ሲያዳምጡ

በፋልኮን ግዛት ያለ አንድ ጉባኤ የሚገኘው፣ የስልክም ሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት አካባቢ ነው። በመሆኑም 70 የሚያህሉት የጉባኤው አስፋፊዎች የመታሰቢያውን በዓል ንግግር በመልእክት መቀበያ ሬዲዮ አማካኝነት ተከታትለዋል።

አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “መተቃቀፍ ወይም ዓይን ለዓይን መተያየት ባንችልም የወንድሞቻችንን ድምፅ መስማት ችለናል። ሁላችንም አብረን ያለን ያህል ሆኖ ተሰምቶናል።”

ከመታሰቢያው በዓል በፊት በነበሩት ቀናት፣ ጉባኤዎች ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች የመታሰቢያውን በዓል እንዲያከብሩ ለመጋበዝ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ሰዎች የመታሰቢያውን በዓል ንግግር ማዳመጥ የሚችሉባቸው የተለያዩ አማራጮች ተዘጋጅተው ነበር። ከ3,000 በላይ የመጋበዣ ወረቀቶች ተሰራጭተዋል። ወንድሞች ያደረጉት ጥረት ግሩም ውጤት አስገኝቷል። ለምሳሌ አራያ በተባለች በባሕር ዳርቻ የምትገኝ መንደር ከመቶ የሚበልጡ ሰዎች የመታሰቢያውን በዓል ንግግር በስልክ ተከታትለዋል።

አንድ ወንድም የመታሰቢያውን በዓል ንግግር በሬዲዮ ሲያዳምጥ

በተጨማሪም የቬኔዙዌላ ቅርንጫፍ ቢሮ የመታሰቢያውን በዓል ፕሮግራም በ82 የሬዲዮ ጣቢያዎችና በዘጠኝ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለማስተላለፍ ዝግጅት አድርጎ ነበር። ቢያንስ 8,000 የሚያህሉ ወንድሞችና ተጋባዥ እንግዶች የመታሰቢያውን በዓል በዚህ መንገድ አክብረዋል። ፕሮግራሙ እንደ ዋራዎ፣ ዋዩናይኪ፣ የኩዋና፣ ጓሂቦ፣ ፑሜ፣ ፒያሮአና ፔሞን ባሉ በአገሪቱ የሚነገሩ ቋንቋዎች ተላልፏል።

በቦሊቫር ግዛት በምትገኝ ጓሲፓቲ የተባለች ከተማ የመታሰቢያው በዓል ንግግር ከምሽቱ 12:30 ጀምሮ ለአንድ ጊዜ ያህል እንዲተላለፍ ታቅዶ ነበር። የሚያሳዝነው ግን በዚያ አካባቢ ብዙ ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ይቋረጣል። በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ሙሉውን የመታሰቢያ በዓል ንግግር ለማዳመጥ ይቸገራሉ የሚል ስጋት ነበር። ሆኖም በሬዲዮ ጣቢያው ባጋጠመ የቴክኒክ ችግር ምክንያት ንግግሩ በዚያ ምሽት እየተደጋገመ ከአሥር ጊዜ በላይ ተላለፈ። በመሆኑም አድማጮች በተለያየ ሰዓት ላይ ሙሉውን ንግግር ማዳመጥ የሚችሉበት አጋጣሚ አገኙ። የደረሰን ሪፖርት እንደሚጠቁመው ከ600 የሚበልጡ ሰዎች ንግግሩን አዳምጠዋል። አንድ ወንድም “ይሖዋ አንድም ሰው ይህን ንግግር ሳይሰማ እንዲቀር አልፈለገም!” በማለት ተናግሯል።

ወንድሞቻችን ‘በልዩ ልዩ ፈተናዎች ቢጨነቁም’ ይሖዋ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበርና ሌሎችን ለመጋበዝ ያደረጉትን ጥረት እንደባረከላቸው በማየታቸው ‘እጅግ ተደስተዋል።’—1 ጴጥሮስ 1:6, 7