በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሴሊም ታገኖቭ

ኅዳር 24, 2020
ቱርክሜኒስታን

በቱርክሜኒስታን የሚኖረው ወንድም ታገኖቭ የአንድ ዓመት የእስራት ፍርዱን ከጨረሰ በኋላ ከእስር ተፈታ

በቱርክሜኒስታን የሚኖረው ወንድም ታገኖቭ የአንድ ዓመት የእስራት ፍርዱን ከጨረሰ በኋላ ከእስር ተፈታ

ወንድም ሴሊም ታገኖቭ ጥቅምት 3, 2020 ከእስር ከተፈታ በኋላ “ይሖዋ፣ ወደ እሱ ስጸልይ እንድረጋጋ በማድረግ ረድቶኛል” ሲል ተናግሯል። ገና የ19 ዓመት ወጣት የሆነው ሴሊም ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ሕሊናው ስላልፈቀደለት አንድ ዓመት ታስሮ ተፈቷል።

ሴሊም የተወለደው በቱርክሜኒስታን ዋና ከተማ በአሽገባት ነው። ከትንሽነቱ ጀምሮ ጎበዝ ተማሪና ለሙዚቃ ፍቅር የነበረው ልጅ ነው። ሴሊም ሙዚቃ ይደርሳል፣ ይዘፍናል እንዲሁም ጊታር ይጫወታል። ወላጆቹ፣ ሁለት ወንድሞቹና ጓደኞቹ ሴሊም ደግ፣ ጨዋና ደስተኛ እንደሆነ ይናገሩለታል። በሴሊም ላይ ጥፋተኛ ነህ የሚል ብይን ከመተላለፉ በፊት ፍርድ ቤቱ ያቆመለት ጠበቃ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ጥሩ ባሕርይ ያለው ጨዋ ልጅ ነው፤ አያጨስም ወይም አይሰክርም፤ በዚያ ላይ ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ማጠናቀቁ ነው። በዚህ ልጅ ላይ እስራት መፍረድ ሕይወቱን ማበላሸት ነው።”

የእስር ቤት ሕይወት ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ሴሊም እንዲህ ብሏል፦ “እስር ቤት ባሳለፍኩት ጊዜ ከይሖዋ ጋር ያለኝ ዝምድና ተጠናክሯል። ቤት ሳለሁ የተማርኳቸውን መንፈሳዊ እውነቶች ለማስታወስ ጥረት አደርግ ነበር፤ ይህም ስለ እነዚህ እውነቶች ጥልቀት ያለው ግንዛቤ እንዲኖረኝ ረድቶኛል። እንደ ኢሳይያስ 41:10, 11 ያሉትን ጥቅሶች ማስታወሴም አበረታቶኛል።

“ጉዳዬ እስኪታይ ጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት የማነጋግረው ወይም ጭንቀቴን የሚጋራኝ ሰው ስላልነበር ከብዶኝ ነበር። ሆኖም ይሖዋ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። ከዚያ በኋላ፣ መጀመሪያ ላይ ይጠሉኝና ያስፈራሩኝ የነበሩ እስረኞችና የእስር ቤት ጠባቂዎች ይደግፉኝና ያበረታቱኝ ጀመር። ይህን ማየቴ ይሖዋ እየደገፈኝ እንዳለ አረጋግጦልኛል።”

ሴሊም በአካባቢው ያሉ ወንድሞችና እህቶች ባደረጉለት ነገርም ተበረታትቷል። በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ታስሬ እያለሁ ብዙዎች ሰላምታና የሚያበረታቱ ሐሳቦች ይልኩልኝ ነበር። እነዚህን ሐሳቦች በቃሌ ለመያዝ ጥረት አደርግ ነበር፤ ከዚያም እደጋግማቸዋለሁ። ትልቅ ማበረታቻና ማጽናኛ ሆነውልኛል።”

በቱርክሜኒስታን ሕግ መሠረት ሴሊም እንደገና ለወታደራዊ አገልግሎት ሊጠራም ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ከአሁኑ ረዘም ያለ ጊዜ እስራት ሊፈረድበት እንደሚችል ሴሊም ያውቃል። ሆኖም እንዲህ ብሏል፦ “በይሖዋ እርዳታ ይህን ፈተና ማለፌ ፍርሃቴን አጥፍቶልኛል። ይሖዋ የሚያደርግልኝ ድጋፍ ደፋርና ልበ ሙሉ እንደሆን አድርጎኛል።”

ሁላችንም ወደፊት ከባድ ፈተና ሊያጋጥመን እንደሚችል እንጠብቃለን። ሴሊም እንዲህ ሲል አበረታቶናል፦ “ወደፊት እንዲህ ዓይነት ፈተና የሚያጋጥማችሁ ሁሉ ‘ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ’ የሚለውን ኢሳይያስ 30:15⁠ን አስታውሱ።”