በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ማክሳት ጁማዱርዲየቭ

ጥር 28, 2021
ቱርክሜኒስታን

ወንድም ማክሳት ጁማዱርዲየቭ በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለሁለተኛ ጊዜ ታሰረ

ወንድም ማክሳት ጁማዱርዲየቭ በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለሁለተኛ ጊዜ ታሰረ

የፍርድ ውሳኔ

ጥር 18, 2021 የቱርክሜኒስታን ፍርድ ቤት ወንድም ማክሳት ጁማዱርዲየቭ ጥፋተኛ ነው ብሎ ፈረደበት። ይህ ወንድም በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የሁለት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

አጭር መግለጫ

ማክሳት ጁማዱርዲየቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 2000 (ሴይዲ፣ ሌባፕ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ ሁለት እህቶች አሉት። ጎበዝ ተማሪ ነው። በስፖርታዊ ጨዋታዎች መካፈል ያስደስተዋል። የተዋጣለት ሠዓሊ ነው። በአካባቢው የሚታወቀው ትሑት፣ ሐቀኛና ታታሪ ሠራተኛ በመሆኑ ነው

    በ2018 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ2019 ተጠመቀ። ከቤተሰቡ መካከል የይሖዋ ምሥክር የሆነው እሱ ብቻ ነው

የክሱ ሂደት

ወንድም ማክሳት ጁማዱርዲየቭ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከዚህ ቀደም አንድ ዓመት ታስሮ ነበር። ሐምሌ 17, 2019 ከእስር ተፈታ። በቱርክሜኒስታን፣ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ለሁለተኛ ጊዜ ክስ ሊመሠረትባቸው ይችላል፤ በመሆኑም ወንድም ማክሳት ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ መጋቢት 2020 ለሁለተኛ ጊዜ ተጠራ። እሱም በወታደራዊ አገልግሎት እንደማይካፈል የሚገልጽ ደብዳቤ አስገባ፤ ይህን ያደረገው ለሁለተኛ ጊዜ ሊታሰር እንደሚችል እያወቀ ነው።

ባለሥልጣናቱ በተደጋጋሚ ጊዜ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው በጥያቄ ካፋጠጡት እንዲሁም የሕክምና ምርመራ እንዲያደርግ ካደረጉ በኋላ ታኅሣሥ 30, 2020 ሌላ የወንጀል ክስ እንደተመሠረተበት አሳወቁት። በተጨማሪም ፓስፖርቱን ቀሙት።

ወንድም ማክሳት እንደገለጸው የመጀመሪያው የፍርድ ሂደትና እስራቱ በጣም ከባድ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በ2018 ስታሰር በጣም የከበደኝ ከወላጆቼ መለየቱ ነበር። . . . ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ስላልሆኑ ይህን ውሳኔ ካደረግኩ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደማያደርጉልኝ ነግረውኝ ነበር።”

ማክሳት እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “የቤተሰቤንና የጓደኞቼን ናፍቆት ለመቋቋም የረዳኝ በማርቆስ 10:29, 30 ላይ ያለው ሐሳብ ነው። ኢየሱስ፣ ስለ እሱና ስለ ምሥራቹ ስንል ማንኛውንም ነገር ብናጣ መቶ እጥፍ መልሰን እንደምናገኝ ተናግሯል።”

ማክሳት ታስሮ በነበረበት ጊዜ፣ ሲጸልይ ይሖዋ ቶሎ ምላሽ እንደሚሰጠውና ካጋጠመው ችግር መውጫ እንደሚያዘጋጅለት አስተውሎ ነበር። ማክሳት ኢያሱ 1:9⁠ን ብዙ ጊዜ ያስታውስ እንደነበረ ገልጿል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ደፋርና ብርቱ ሁን . . . አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር ስለሆነ አትሸበር፤ አትፍራ።”

ማክሳት ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናውን ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረገ ገልጾ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ለሁለተኛ ጊዜ መታሰር ቢኖርብኝም እንኳ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ይሖዋ እንደሚረዳኝ እምነት አለኝ። በፊልጵስዩስ 4:6, 7 ላይ የሚገኘው ምክር ደፋር እንድሆንና እንድረጋጋ ይረዳኛል።”

ለወንድማችን ማክሳት እንዲሁም የይሖዋን ሉዓላዊነት በታማኝነት እየደገፉ ላሉ ሌሎች ደፋር ወጣቶች መጸለያችንን እንቀጥላለን። ይሖዋ በእስር ላይ የሚገኙትን እነዚህን ታማኝ ወንድሞቻችንን በእጅጉ እንደሚክሳቸው እርግጠኞች ነን።—ራእይ 2:10