ጥር 11, 2021
ቱርክሜኒስታን
ወንድም ሩስላን አርትየክማየራዶቭ በሕሊናው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለሁለተኛ ጊዜ እስራት ሊፈረድበት ይችላል
የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን
የቱርክሜኒስታን ወታደራዊ ፍርድ ቤት የወንድም ሩስላን አርትየክማየራዶቭን ጉዳይ ተመልክቶ በቅርቡ a ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል። ወንድም ሩስላን በሕሊናው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ እስከ ሁለት ዓመት ሊታሰር ይችላል። ከታኅሣሥ 15, 2020 ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውሏል። በገለልተኝነት አቋሙ ምክንያት ፍርድ ቤት ሲቀርብ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ሲሆን እስራት ሊፈረድበት ይችላል።
አጭር መግለጫ
ሩስላን አርትየክማየራዶቭ
የትውልድ ዘመን፦ 2000 (አልፓን ጌንጌሽሊክ መንደር)
ግለ ታሪክ፦ ያደገው በገጠራማ አካባቢ ነው። ጋራዥ ውስጥ ይሠራ ነበር። ጎበዝ ተማሪ የነበረ ሲሆን እግር ኳስ መጫወት ይወዳል
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን የተማረው ከእናቱ ነው። በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለው ፍቅርና አንድነት ስለማረከው በ2015 በ15 ዓመቱ ተጠመቀ። በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ እንዳይሆን ያደረገው ለይሖዋ አምላክ ያለው ፍቅር ነው
የክሱ ሂደት
ወንድም ሩስላን አርትየክማየራዶቭ በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነሐሴ 13, 2018 የአንድ ዓመት እስራት ተፈረደበት፤ በወቅቱ 18 ዓመቱ ነበር። ነሐሴ 12, 2019 የእስራት ጊዜውን አጠናቅቆ ተፈታ።
በቱርክሜኒስታን ሕግ መሠረት፣ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ወጣት ወንዶች ለሁለተኛ ጊዜ ክስ ሊመሠረትባቸው ይችላል። በመሆኑም ኅዳር 2020 ሩስላን ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሰጥ በድጋሚ ተጠራ።
ሩስላን ለሁለተኛ ጊዜ ሊታሰር እንደሚችል ቢያውቅም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን በድጋሚ ገለጸ። ታኅሣሥ 15, 2020 የተያዘ ሲሆን ፍርድ ቤት እስኪቀርብ ድረስ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደርጓል።
ሩስላን ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ቆርጧል። ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበበትን ጊዜ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “የፍርድ ሂደቱ ከባድ እንደሚሆን እና ኢፍትሐዊ ድርጊት ሊፈጸምብኝ እንደሚችል ባውቅም አልፈራሁም ነበር። ደስታዬን እና መንፈሳዊነቴን በምንም ነገር አልቀይርም።”
ሩስላን በእስር ቤት ያሳለፈው ጊዜ ከባድ ነበር። የታሰረበት ሁኔታ በጣም አስከፊ ነበር፤ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ግፍ ተፈጽሞበታል። ያም ቢሆን የይሖዋ እርዳታ መቼም ቢሆን እንዳልተለየው ተመልክቷል። ሩስላን እንዲህ ብሏል፦ “እስር ቤት በነበርኩበት ወቅት የይሖዋን እጅ በተደጋጋሚ አይቻለሁ። ለምሳሌ፣ ሲደበድቡኝ ሕመሙ የሚሰማኝ የመጀመሪያው ምት ላይ ብቻ ነበር።” በተጨማሪም የአካባቢው ወንድሞችና እህቶች ያደረጉለት ፍቅራዊ እንክብካቤ ሩስላንን ያጠናከረው ከመሆኑም ሌላ በዙሪያው ላሉት ሰዎች ግሩም ምሥክርነት ሰጥቷል።
ሩስላን ለሁለተኛ ጊዜ ሊታሰር እንደሚችል ቢያውቅም ይሖዋ እንደሚረዳው እርግጠኛ ነው፤ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ እንደሚክሰኝ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም። . . . አስተማማኝ ተስፋ ያለው ሰው፣ ደስታው ወደር የለውም፤ ደስታ ደግሞ ጥንካሬና ጽናት ያስገኛል። ጠንካራ ሰው ፈጽሞ አይሰበርም።”
ይሖዋ የትኛውንም ፈተና በድፍረትና በደስታ እንድንቋቋም እንደሚረዳን ያስመሠከሩትን እንደ ሩስላን ያሉ ደፋር ወጣቶች በጣም እናደንቃቸዋለን። ለአምላክ መንግሥት የማይናወጥ ታማኝነት በማሳየታቸው ወሮታቸውን እንደሚያገኙ እርግጠኞች ነን።—ዕብራውያን 11:6
a ፍርድ ቤቱ ብይን የሚያስተላልፍበትን ቀን አስቀድሞ የማያሳውቅበት ጊዜ አለ።