በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ቬኒያሚን ጌንድዥዬቭ

የካቲት 3, 2021
ቱርክሜኒስታን

ወንድም ቬኒያሚን ጌንድዥዬቭ በገለልተኝነት አቋሙ ምክንያት የሁለት ዓመት እስራት ተፈረደበት

ወንድም ቬኒያሚን ጌንድዥዬቭ በገለልተኝነት አቋሙ ምክንያት የሁለት ዓመት እስራት ተፈረደበት

የፍርድ ውሳኔ

ወንድም ቬኒያሚን ጌንድዥዬቭ በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የቱርክሜኒስታን ፍርድ ቤት ጥር 19, 2021 የሁለት ዓመት እስራት ፈረደበት።

አጭር መግለጫ

ቬኒያሚን ጌንድዥዬቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 2000 (ሴይዲ)

  • ግለ ታሪክ፦ ያደገው በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ነው። በ15 ዓመቱ አስፋፊ ሆነ። በ19 ዓመቱ ተጠመቀ። ገርና ተጫዋች በመሆኑ ይታወቃል

    የመኪና ጥገና ሥልጠና ወስዷል። ጊታር መጫወት ይወዳል። አብረውት የሚማሩት ልጆች በእምነቱ ምክንያት ያሾፉበት ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለተመሠረተው እምነቱ እንዴት ጥብቅና መቆም እንደሚችል ተምሯል

የክሱ ሂደት

ቬኒያሚን በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሐምሌ 2018 የአንድ ዓመት እስራት ተፈርዶበት ነበር። ሰኔ 25, 2019 ከእስር ቤት ተፈታ።

ታኅሣሥ 25, 2020 በዳኖ አውራጃ ወደሚገኘው የአቃቤ ሕግ ቢሮ ተጠራ። ባለሥልጣናቱ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነበትን ምክንያት በጽሑፍ እንዲያቀርብ ጠየቁት። ታኅሣሥ 30, 2020 የአቃቤ ሕግ ቢሮው ለሁለተኛ ጊዜ የወንጀል ክስ እንደተመሠረተበት ለቬኒያሚን አሳወቀው። ከዚያም ቬኒያሚን ፓስፖርቱን ተነጠቀ።

ቬኒያሚን ለመጀመሪያ ጊዜ በታሰረበት ወቅት ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ እየረዳኝ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ይሖዋ ብርታት ሰጥቶኛል፤ እምነቴንም አጠናክሮልኛል። ወደ ይሖዋ እጸልይ እንዲሁም ምሥራቹን አብረውኝ ለታሰሩ ሰዎች እናገር ነበር፤ ይህም ተስፋ እንዳልቆርጥ ረድቶኛል።

“እስር ቤት ሳለሁ፣ መጥተው ሊጠይቁኝ ያልቻሉ ወንድሞችን ሰላምታ ወላጆቼ ይነግሩኝ ነበር። እንዲህ ያለው ድጋፍ የእስራት ጊዜዬን እስክጨርስ ድረስ እንድጸና ረድቶኛል።”

ቬኒያሚንን ካበረታቱት ጥቅሶች አንዱ ኢሳይያስ 54:17 ነው። ጥቅሱ በከፊል “አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል” ይላል። እንዲህ ዓይነቶቹ ጥቅሶች እንዲሁም እኛ የምናቀርበው ጸሎት አሁን ያጋጠመውን የእምነት ፈተናም በጽናት ለመወጣት ይረዳዋል።