የካቲት 11, 2021
ቱርክሜኒስታን
ወንድም ናዛር አሊየቭ በሕሊናው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ የአንድ ዓመት እስራት ተፈረደበት
የፍርድ ውሳኔ
የካቲት 10, 2021 የቱርክሜኒስታን ፍርድ ቤት፣ ወንድም ናዛር አሊየቭ በሕሊናው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ የአንድ ዓመት እስራት ፈርዶበታል።
አጭር መግለጫ
ናዛር አሊየቭ
የትውልድ ዘመን፦ 2000 (ሌባፕ ክልል)
ግለ ታሪክ፦ የሚኖረው ከእናቱና ከሁለት እህቶቹ ጋር በቱርክሜናባት ነው። መረብ ኳስ እና እግር ኳስ መጫወት ይወዳል። ሁለት ዓይነት የልብ ሕመም አለበት። ቤተሰቡን በቁሳዊ ለመደገፍ ፀጉር አስተካካይ ሆኖ ይሠራል
ለመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ፍቅር እንዲያዳብር የረዳችው እናቱ ነች። በ2015 በ14 ዓመቱ ተጠመቀ። ደስተኛ፣ ለጋስና ትሑት በመሆኑ ይታወቃል። ቤተሰቦቹ የገለልተኝነት አቋሙን ይደግፋሉ
የክሱ ሂደት
ወንድም ናዛር አሊየቭ ግንቦት 16, 2020 ወደ ውትድርና ምልመላ ቢሮ ተወሰደ። ባለሥልጣናቱ ምልመላውን መቀበሉን ለማሳየት ወታደራዊ የደንብ ልብስ እንዲለብስ ሊያስገድዱት ሞከሩ፤ እሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም። ግንቦት 28 ናዛር እንደገና ባለሥልጣናቱ ፊት የቀረበ ሲሆን ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን በድጋሚ ገለጸ። በቀጣዩ ወር ናዛር ሃይማኖታዊ አቋሙን ለማብራራት ለአውራጃው የምልመላ ቢሮ ደብዳቤ ጻፈ።
ጥር 4, 2021 ናዛር እና እናቱ በኮጃምባዝ አውራጃ ወደሚገኘው የአቃቤ ሕግ ቢሮ ሄዱ። ናዛር ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነው ለምን እንደሆነ ከገለጸ በኋላ አማራጭ አገልግሎት መስጠት ይችል እንደሆነ ጠየቀ። ያም ቢሆን መርማሪው በናዛር ላይ ክስ እንደሚመሠረትበት ገለጸ።
የ20 ዓመቱ ናዛር እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች ውስጥ በይሖዋ ስትታመኑ እሱ ውስጣዊ ሰላም ይሰጣችኋል። በይሖዋ እርዳታ ተረጋግታችሁ መናገር ትችላላችሁ።”
አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ያጋጠሙኝን ነገሮች መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ ሁልጊዜ እንደደገፈኝ እገነዘባለሁ። ይህም ይሖዋ ወደፊትም እንደሚረዳኝ እንድተማመን ያደርገኛል።”
ቱርክሜኒስታን ውስጥ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ዝግጅት የለም። በመሆኑም በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ወንድሞች እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ እስራት ሊፈረድባቸው ይችላል። በአሁኑ ወቅት ቱርክሜኒስታን ውስጥ በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት እስር ቤት የሚገኙ 15 ወጣት ወንድሞች አሉ።
ይሖዋ ለናዛርም ሆነ በቱርክሜኒስታን ለሚገኙ ሌሎች ወንድሞቻችን ‘ታማኝ እንደሚሆንላቸው’ እንተማመናለን።—መዝሙር 18:25