የካቲት 8, 2021
ቱርክሜኒስታን
ወንድም አርተር ያንጊባዬቭ በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለሁለተኛ ጊዜ ቅጣት ተበየነበት
የፍርድ ውሳኔ
ወንድም አርተር ያንጊባዬቭ በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የቱርክሜኒስታን ፍርድ ቤት ጥር 18, 2021 የሁለት ዓመት እስራት ፈረደበት። የገለልተኝነት አቋም በመያዙ ምክንያት ቅጣት ሲበየንበት ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው።
አጭር መግለጫ
አርተር ያንጊባዬቭ
የትውልድ ዘመን፦ 1997 (ሴይዲ)
ግለ ታሪክ፦ አርተር በልጅነቱ ብዙ ችግሮች አጋጥመውት ነበር፤ ይህም በዓለም ላይ ግፍ የተስፋፋው ለምን እንደሆነ እንዲጠይቅ አነሳሳው። የይሖዋ ምሥክር ከሆነችው እህቱ ጋር በዚህ ጥያቄ ላይ መወያየት ጀመረ። ከዚያም በ13 ዓመቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ2014 ተጠመቀ
ሥራው አፓርታማዎችን ማደስ ነው። የአርተር ወላጆች ልጃቸው ደግና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንደሆነ ይናገራሉ። ጎረቤቶቹም ሐቀኛ በመሆኑ ያከብሩታል
የክሱ ሂደት
አርተር በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነሐሴ 8, 2016 በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን ፍርድ ቤት እስኪቀርብ ድረስ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ። ነሐሴ 30 ለሁለት ዓመት ያህል የጉልበት ሥራ እንዲሠራ ተፈረደበት። መስከረም 2018 አርተር የተፈረደበትን ቅጣት አጠናቀቀ።
ታኅሣሥ 15, 2020 ለሁለተኛ ጊዜ ለውትድርና አገልግሎት ተመለመለ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ለምርመራ ወደ አቃቤ ሕግ ቢሮ የተጠራ ሲሆን ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነበትን ምክንያት በጽሑፍ እንዲያቀርብ ተጠየቀ።
ታኅሣሥ 30 የአቃቤ ሕግ ቢሮው ለሁለተኛ ጊዜ የወንጀል ክስ እንደተመሠረተበት ለአርተር አሳወቀው። ከዚያም ፓስፖርቱን ተነጠቀ።
አርተር የመጀመሪያው ብይን ከተላለፈበት በኋላ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በሮም 8:37-39 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለይሖዋ ታማኝ ከመሆን ማንም ሊያግደኝ እንደማይችል እንድተማመን ረድቶኛል።” በይሖዋ እርዳታ አርተር ይሄኛውንም ፈተና በጽናት መቋቋም እንደሚችል እንተማመናለን።