በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ኅዳር 3, 2020
ቱርክሜኒስታን

ወንድም ፔትሮሶቭ በቱርክሜኒስታን ለአንድ ዓመት ከታሰረ በኋላ ተለቀቀ

ወንድም ፔትሮሶቭ በቱርክሜኒስታን ለአንድ ዓመት ከታሰረ በኋላ ተለቀቀ

ዴቪድ ፔትሮሶቭ በቱርክሜኒስታን የሚኖር የ19 ዓመት ወጣት ወንድም ነው። ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ቢሆንም እምነቱን በእጅጉ የሚፈትን ሁኔታ አጋጥሞታል፤ በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለአንድ ዓመት ከታሰረ በኋላ መስከረም 30, 2020 ከእስር ተለቋል።

ወንድም ፔትሮሶቭ እንዲህ ብሏል፦ “እስር ላይ ሳለሁ የምቆዝምባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት አጽናንቶኛል። ይሖዋ ስሜቴን እንደሚረዳና እኔን ለማጽናናት ፈቃደኛ እንደሆነ ማወቄ ወደ እሱ እንድጸልይ አነሳስቶኛል። የተለያዩ ጥቅሶች በዚያ ያጋጠሙኝን ሁኔታዎች እንድቋቋም ረድተውኛል፤ በተለይ በፊልጵስዩስ 4:13 ላይ ብዙ ጊዜ አሰላስል ነበር።”

ወንድም ፔትሮሶቭ የተወለደው የቱርክሜኒስታን ዋና ከተማ በሆነችው በአሽጋባት ነው። በልጅነቱ ጊታር መጫወት የተማረ ሲሆን ሙዚቃ ማቀናበር ይወዳል። በተጨማሪም ኳስ መጫወት፣ ተራራ መውጣትና በአካባቢው በሚገኙ ሐይቆች መዋኘት ያስደስተዋል።

አብሮት ይማር ከነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ካጠና በኋላ በ2019 ተጠመቀ። የፔትሮሶቭ ቤተሰቦች የይሖዋ ምሥክሮች ባይሆኑም በአምላክ ላይ ያለውን እምነትና አቋሙን ያከብሩለታል።

ፔትሮሶቭ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ፍርድ ቤት ቀረበ። ቱርክሜኒስታን በወታደራዊ አገልግሎት ለማይካፈሉ ሰዎች የሲቪል አገልግሎት አማራጭ አታቀርብም። በዚህ የተነሳ የአንድ ዓመት እስር ተፈረደበት።

ወንድም ፔትሮሶቭ ታስሮ በነበረበት ጊዜ ይሖዋ የሚያስፈልገውን ድጋፍ አድርጎለታል። እንዲህ ብሏል፦ “እስር ላይ ሳለሁ እናቴ መጥተው ሊጠይቁኝ ያልቻሉ ወንድሞችና እህቶች ሰላምታ እንደላኩልኝ እና አዘውትረው እንደሚጸልዩልኝ ትነግረኝ ነበር። ይህ በጣም አስደስቶኛል።”

በቱርክሜኒስታን ሕግ መሠረት፣ ወንድም ፔትሮሶቭ ለሁለተኛ ጊዜ ለወታደራዊ አገልግሎት ሊመለመል እንደሚችል ያውቃል። ይህ ሕግ እሱ ላይ ተግባራዊ ከተደረገ ጥፋተኛ ተብሎ ሊፈረድበትና ከባድ የእስር ቅጣት ሊተላለፍበት ይችላል።

ፔትሮሶቭ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ ድጋሚ መታሰር አልፈልግም፤ ግን አልፈራም። በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነት፣ ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም መንፈሳዊ መዝሙሮች እንዳልረበሽና ደፋር እንድሆን ረድተውኛል።”

ወደፊትም ቢሆን ይሖዋ ወንድም ፔትሮሶቭን ደፋር እንዲሆን እንደሚረዳውና እምነቱን እንደሚያጠናክርለት እንተማመናለን። በተጨማሪም ቱርክሜኒስታን ውስጥ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ለታሰሩ አሥር ወንድሞች መጸለያችንን እንቀጥላለን። ይሖዋ እንደሚወዳቸው፣ እንደሚያስባቸውና እንደሚደግፋቸው እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 69:33