በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ወንድማማቾቹ ኤልዶር ሳቡሮቭ እና ሳንጃርቤክ ሳቡሮቭ

ነሐሴ 7, 2020
ቱርክሜኒስታን

የቱርክሜኒስታን ፍርድ ቤት በወንድም ኤልዶር ሳቡሮቭ እና ሳንጃርቤክ ሳቡሮቭ ላይ የሁለት ዓመት እስራት ፈረደባቸው

የቱርክሜኒስታን ፍርድ ቤት በወንድም ኤልዶር ሳቡሮቭ እና ሳንጃርቤክ ሳቡሮቭ ላይ የሁለት ዓመት እስራት ፈረደባቸው

የቱርክሜኒስታን ፍርድ ቤት ወንድም ኤልዶር ሳቡሮቭ እና ወንድም ሳንጃርቤክ ሳቡሮቭ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ የሁለት ዓመት እስራት በይኖባቸዋል። ኤልዶር 21 ዓመቱ ሲሆን ሳንጃርቤክ ደግሞ 25 ዓመቱ ነው። ፍርድ ቤቱ እነዚህ ወንድማማቾች ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አድርጎታል። ሁለቱም በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት የተፈረደባቸው ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

በ2016 ወንድም ሳንጃርቤክ ሳቡሮቭ የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆነ በአክብሮት ገልጾ ነበር። በዚህም ምክንያት ክስ ቀርቦበት ለሁለት ዓመት በአመክሮ እንዲቆይ ተወስኖበታል።

በቀጣዩ ዓመት ደግሞ የሳንጃርቤክ ታናሽ ወንድም ኤልዶር በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ እንዳልሆነ ገለጸ። በውጤቱም ለሁለት ዓመት ያህል የጉልበት ሥራ እንዲሠራና ከደሞዙ ላይ 20 በመቶው ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን ተበይኖበታል።

በቱርክሜኒስታን ሕግ መሠረት በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች በዚህ አቋማቸው እስከቀጠሉ ድረስ ለሁለተኛ ጊዜ በወንጀል ሊጠየቁ ይችላሉ። ሚያዝያ 2020 ለውትድርና አገልግሎት የሚመለምለው መሥሪያ ቤት ለእነዚህ ወንድሞች በድጋሚ ጥሪ አቅርቦላቸው ነበር። ሆኖም ሁለቱም የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። በመሆኑም ጥፋተኛ ናቸው ተብለው እስር ቤት ገብተዋል።

የወንድማማቾቹ ወላጆች በልጆቻቸው መታሰር ምክንያት ከሚሰማቸው ጥልቅ ሐዘን በተጨማሪ ከዚህ ጋር ተያይዘው ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችም ያጋጥሟቸዋል። አባታቸው ከባድ የጀርባ ሕመም ስላለበት ሥራ መሥራት አይችልም። ልጆቹ ጥጥ በማምረት ቤተሰቡን ይደጉሙ ነበር። አሁን ግን እስር ቤት ስለገቡ ለወላጆቻቸው ቁሳዊ ድጋፍ የሚያደርግላቸው የለም። እንዲያውም ወላጆቻቸው ለታሰሩት ልጆቻቸው የሚያስፈልጓቸውን አንዳንድ ነገሮች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

ቱርክሜኒስታን በወታደራዊ አገልግሎት ለማይካፈሉ ሰዎች የሲቪል አገልግሎት አማራጭ አታቀርብም። በዚህም የተነሳ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ወጣት ወንድሞች ከአንድ እስከ አራት ዓመት የሚዘልቅ እስራት ይፈረድባቸዋል። እነዚህን ወንድማማቾች ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ ቱርክሜኒስታን ውስጥ በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት የታሰሩ አሥር ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ።

ይሖዋ በቱርክሜኒስታን ያሉ ወጣት ወንድሞቻችንን ላሳዩት ድፍረት እንደሚባርካቸው እርግጠኞች ነን። ሁሉም ይሖዋ ለንጉሥ አሳ የተናገረውን “የድካማችሁን ዋጋ ስለምታገኙ በርቱ፤ ተስፋም አትቁረጡ” የሚለውን ሐሳብ እንዲያስታውሱ ምኞታችን ነው።—2 ዜና መዋዕል 15:7