በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሴርዳር ዶቭሌቶቭ፣ ሰኔ 2019

ታኅሣሥ 9, 2019
ቱርክሜኒስታን

የቱርክሜኒስታን ፍርድ ቤት በወንድም ዶቭሌቶቭ ላይ የሦስት ዓመት እስር በየነ

የቱርክሜኒስታን ፍርድ ቤት በወንድም ዶቭሌቶቭ ላይ የሦስት ዓመት እስር በየነ

ኅዳር 12, 2019 የቱርክሜኒስታን ፍርድ ቤት በ26 ዓመቱ ወንድም ሴርዳር ዶቭሌቶቭ ላይ የሦስት ዓመት እስር በየነ። ወንድም ዶቭሌቶቭ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ባለመስጠታቸው እስር ከተፈረደባቸው አሥር የቱርክሜኒስታን ወንድሞች መካከል አንዱ ነው። ሰባቱ ወንድሞች እስር የተፈረደባቸው በ2019 ሲሆን ሦስቱ ደግሞ በ2018 ነው። እነዚህ ወንድሞች ከአንድ ዓመት እስከ አራት ዓመት የሚዘልቅ የተለያየ ርዝማኔ ያለው እስር ተበይኖባቸዋል።

ወንድም ዶቭሌቶቭ የሚኖረው በደቡብ ምሥራቅ ቱርክሜኒስታን፣ ሜሪ ክልል በምትገኘው በባይራማሊ ከተማ ነበር። ባለቤቱ ሱርያ እና እናቱ ሶንያም የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።

የወንድም ዶቭሌቶቭ ክስ በፍርድ ቤት መታየት የጀመረው ኅዳር 11, 2019 ነበር። ወንድም ዶቭሌቶቭ በሃይማኖታዊ እምነቱ ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው እንደማይፈቅድለት ለፍርድ ቤቱ ገልጿል። በተጨማሪም ሦስት ሐኪሞች ወንድም ዶቭሌቶቭ ከባድ የአንጀት ችግር ስላለበት ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ ሊሆን እንደሚገባ መሥክረው ነበር።

እነዚህ ማስረጃዎች ቢቀርቡም ዳኛው ወንድም ዶቭሌቶቭ ከወታደራዊ አገልግሎት ለማምለጥ “እንዳጭበረበረ” በመግለጽ ወደ ማረሚያ ቤት ልከውታል። ወንድም ዶቭሌቶቭ በሌባፕ ክልል ውስጥ በሚገኘው በበረሃማው ሴይዲ ካምፕ ከታሰሩት ዘጠኝ ወንድሞች ጋር በቅርቡ እንደሚቀላቀል ይጠበቃል። ወንድም ዶቭሌቶቭ ይግባኝ ለመጠየቅ ወስኗል።

በቱርክሜኒስታን የሚገኙ ወንድሞቻችን ግፍ እየደረሰባቸውም ቢሆንም ይሖዋ ድፍረትና ታማኝነት የሚያሳዩ አገልጋዮቹን እንደሚባርካቸው በገባው ቃል በመተማመን ለወንድሞቻችን መጸለያችንን እንቀጥላለን።—መዝሙር 37:18, 24