በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ኤዚዝ አታባዬቭ ከእስር ከተፈታ በኋላ

ጥር 14, 2021
ቱርክሜኒስታን

“ይህን ፈተና የተቋቋምኩት በይሖዋ እርዳታ ነው”

“ይህን ፈተና የተቋቋምኩት በይሖዋ እርዳታ ነው”

በቱርክሜኒስታን የሚኖረው ወንድም ኤዚዝ አታባዬቭ በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ለሁለት ዓመት ታስሮ ነበር። ታኅሣሥ 19, 2020 ከእስር ተፈቷል። ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በቱርክሜኒስታን በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው 46 ወንድሞች ታስረዋል።

ወንድም ኤዚዝ አታባዬቭ በ2016 ለወታደራዊ አገልግሎት ተመለመለ። እሱም ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው እንደማይፈቅድለት ገለጸ። ከዚያም ጉዳዩ ወደ ከተማው አቃቤ ሕግ ቢሮ ተላከ። ከሁለት ዓመታት ገደማ በኋላ ኤዚዝ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተጠራ። ታኅሣሥ 19, 2018 ፍርድ ቤቱ የሁለት ዓመት እስራት በየነበት።

ኤዚዝ እንዲህ ብሏል፦ “ከመታሰሬ በፊት እንደ እኔ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠማቸውን ወይም ታስረው የተፈቱ ብዙ ወንድሞችን አነጋግሬ ነበር፤ እነሱም ምን መጠበቅ እንዳለብኝ ነገሩኝ። በተጨማሪም በጽሑፎቻችን ላይ የወጡ የሕይወት ታሪኮችን አነበብኩ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ የሚያበረታቱ ሐሳቦችንም አነበብኩ።

“ለፍርድ በቀረብኩበት ቀን አንድ ወንድም ኢሳይያስ 30:15⁠ን አሳየኝ፤ ጥቅሱ ‘ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ’ ይላል። ይህ ጥቅስ ሳልረበሽ እንድኖርና በማንኛውም ጉዳይ በይሖዋ እንድታመን ረድቶኛል። በዚህ ጥቅስ ላይ ማሰላሰሌ በእስር በቆየሁበት ጊዜ ሁሉ ረድቶኛል።”

በእስር ቤት የነበረው ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም ኤዚዝን በጣም የከበደው ግን ከቤተሰቡ መለየቱ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እስር ቤት ሳለሁ አብረውኝ ከታሰሩ መንፈሳዊ ወንድሞቼ ጋር ይበልጥ ተቀራረብኩ። እነሱ እውነተኛ ወዳጆች ሆነውልኛል፤ እንዲሁም የቤተሰቤንና የጓደኞቼን ናፍቆት መቋቋም እንድችል ረድተውኛል።”

ከዚህም ሌላ ኤዚዝ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ ይመሠክር ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ አካባቢ ስለ እምነቴ ለሌሎች ስናገር አንዳንድ እስረኞች ይቃወሙኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ይቃወሙኝ የነበሩት እስረኞችም መልእክቱን ለማዳመጥ ፈቃደኞች ሆኑ። አዳዲስ እስረኞችም ስሰብክ ሲያዩኝ መጀመሪያ ላይ ይቃወሙኝ ነበር። ሆኖም አስቀድሜ የመሠከርኩላቸው የቆዩ እስረኞች ከእኔ ጎን ይቆማሉ፤ እንዲሁም ያስተማርኳቸውን ነገር ለአዲሶቹ እስረኞች ይነግሯቸዋል።”

ኤዚዝ ወደፊት ለሚያጋጥሙን ፈተናዎች ለመዘጋጀት ምን ማድረግ እንዳለብን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ጥልቀት ያለው የግል ጥናት ማድረግና የልብን አውጥቶ ለይሖዋ በግልጽ መንገር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማኛል። የሚያሳስባችሁንና የሚያስፈራችሁን ነገር እንዲሁም ስሜታችሁን ግልጥልጥ አድርጋችሁ ለይሖዋ ንገሩት።

“ይህን ፈተና የተቋቋምኩት በይሖዋ እርዳታ ነው። ከዚህ በኋላም ቢሆን ይሖዋ እንደሚረዳኝ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም። ወደፊት የሚያጋጥሙኝን ፈተናዎች አልፈራም።”—መዝሙር 118:6