ታኅሣሥ 31, 2021
ታይላንድ
መጠበቂያ ግንብ ወደ ታይ ቋንቋ መተርጎም ከጀመረ 75 ዓመታት ተቆጠሩ
“በይሖዋ በመታመን በትጋት ሥሩ፤ ከዚያም ተርጓሚ ታገኛላችሁ”
ጥር 1, 2022 የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ እትም ወደ ታይ ቋንቋ ከተተረጎመ 75 ዓመት ሞላው።
ምሥራቹ ታይላንድ የደረሰው በ1931 ነው። የስብከቱ ሥራ እንደተጀመረ አካባቢ ወንድሞች በቻይንኛ፣ በእንግሊዝኛና በጃፓንኛ በሺዎች የሚቆጠሩ ጽሑፎችን አበርክተዋል። በወቅቱ ወደ ታይ የተተረጎመው ብቸኛው ጽሑፍ ጥበቃ የተባለው ቡክሌት ነበር።
በአገሪቱ የሚያገለግሉት የውጭ አገር ዜጋ የሆኑት ሦስት አቅኚ ወንድሞች የሰዎችን ልብ ለመንካት ተጨማሪ ጽሑፎችን ወደ ታይ ቋንቋ መተርጎም እንደሚያስፈልግ ተገነዘቡ። ወንድም ዊሊ ኡንግላውቤ ወንድም ራዘርፎርድ ጋር በመጻፍ እርዳታ ጠየቀ። ወንድም ራዘርፎርድም “በይሖዋ በመታመን በትጋት ሥሩ፤ ከዚያም ተርጓሚ ታገኛላችሁ” በማለት መለሰለት።
ታኅሣሥ 1939 ወንድም ኩርት ግሩበር እና ወንድም ዊሊ ኡንግላውቤ በሰሜን ታይላንድ እየሰበኩ ነበር። በቺያንግ ማይ በሚገኘው የፕሪስባይቴሪያን የሴቶች ትምህርት ቤት ውስጥ ርዕሰ መምህርት ሆና የምትሠራው ቾምቻይ ኢንታፓን ወንድሞች ያሰራጩትን ጽሑፍ በአጋጣሚ አገኘች። እንግሊዝኛና ታይ አቀላጥፋ የምትናገረው ቾምቻይ እውነትን እንዳገኘች እርግጠኛ ሆነች።
ብዙም ሳይቆይ ቾምቻይ ከምትሠራበት ትምህርት ቤትም ሆነ ከቤተክርስቲያኑ ለቀቀች፤ ተቃውሞ ቢያጋጥማትም እንዲሁም ትምህርት ቤቱ ዳጎስ ያለ ደሞዝ እንደሚከፍላት ቢነግራትም በአቋሟ ጸናች። ከዚያም ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች። ወንድሞች እንድትተረጉም የጠየቋት የመጀመሪያው ጽሑፍ መዳን የተባለው መጽሐፍ ነበር። በኋላም ቾምቻይ በባንኮክ ያለው የቤቴል ቤተሰብ የመጀመሪያ አባላት መካከል አንዷ ሆነች፤ ለበርካታ ዓመታት ብቸኛዋ የታይ ተርጓሚ ሆና አገልግላለች። ከጊዜ በኋላ ተጨማሪ ሴቶች እውነትን ተቀብለው በትርጉም ሥራ እርዳታ አበርክተዋል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ ጽሑፎችን ወደ ታይ ቋንቋ ለመተርጎም የሚደረገው ጥረት ተስተጓጉሎ ነበር፤ ሆኖም ጦርነቱ እንዳበቃ ሥራው በፍጥነት ቀጠለ። የጥር 1947 የመጠበቂያ ግንብ እትም ወደ ታይ የተተረጎመ ሲሆን በሚስዮናውያን ቤት ውስጥ የሚገኘውን የማባዣ መሣሪያ በመጠቀም 200 ቅጂዎች ተዘጋጁ። ይህ የሕትመት ዘዴ እስከ 1952 ድረስ ቀጥሏል፤ በዚያ ወቅት በየወሩ የሚታተሙት ቅጂዎች ብዛት 500 ደርሶ ነበር። ከዚያም ወንድሞች መጽሔቶችን በንግድ ማተሚያ ቤቶች ማሳተም ጀመሩ። መስከረም 1993 የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ በዓለም ዙሪያ የሚሰራጩ የታይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ማተም ጀመረ።
በዛሬው ጊዜ በታይላንድ ቅርንጫፍ ቢሮና በሁለት የርቀት ትርጉም ቢሮዎች የሚገኙ 80 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች በትርጉም ሥራ እየተካፈሉ ነው። መጠበቂያ ግንብ ከታይ በተጨማሪ ወደ ላሁ፣ ሌኦሽኛ፣ የታይ ምልክት ቋንቋ እና አካ በመተርጎም ላይ ይገኛል።
በታይላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ የሚገኙት ከ5,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች መጠበቂያ ግንብ ወደ ቋንቋቸው በመተርጎሙ ይሖዋን ያመሰግናሉ።—ምሳሌ 10:22