በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ግንቦት 20, 2024
ታይላንድ

በባንኮክ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ለአእምሮ ጤና የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አስተዋወቁ

በባንኮክ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ለአእምሮ ጤና የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አስተዋወቁ

ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዝያ 8, 2024 ባንኮክ፣ ታይላንድ ውስጥ 22ኛው የባንኮክ የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ተካሂዷል። በንግሥት ሲሪኪት ብሔራዊ የስብሰባ ማዕከል የተካሄደውን ይህን አውደ ርዕይ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ጎብኝተውታል። ወንድሞቻችን የከፈቱት ኪዮስክ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አእምሮ ጤና እና ጭንቀትን ስለ ማስታገስ እንዲሁም ስለ ሌሎች መሰል ጉዳዮች በሚሰጠው ምክር ላይ ያተኮረ ነበር። በኪዮስኩ ውስጥ ያገለገሉት ወንድሞችና እህቶች ከበርካታ ሰዎች ጋር ውይይት መጀመር ከመቻላቸው በተጨማሪ ከ34 ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

ካወያዩአቸው ሰዎች አንዱ፣ ሴት ልጁ ከባድ የድባቴ ሕመም እንዳለባት ገለጸ። ወንድሞቻችን “የአእምሮ ጤንነት—መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው እርዳታ” የሚል ርዕስ ካለው ቁጥር 1 2023 መጠበቂያ ግንብ ላይ የተወሰዱ የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳቦችን አካፈሉት። በተጨማሪም ከ​jw.org ላይ አስደሳች የቤተሰብ ሕይወትን የሚመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎችን እንዲያገኝ ረዱት። ከመጽሐፍ ቅዱስ ለተሰጠው ተግባራዊ ምክር ከልቡ እንደሚያመሰግናቸው የነገራቸው ሲሆን ሳይውል ሳያድር እነዚህን ምክሮች ለልጁ እንደሚነግራት ገለጸላቸው።

አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ኪዮስካችንን ከጎበኘ በኋላ ከአንደኛው ወንድም ጋር ረዘም ያለ ውይይት አደረገ። የተለያዩ ቪዲዮዎችን jw.org ላይ የተመለከተ ሲሆን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እና ስለሚያከናውኑት መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ ጥያቄዎች ጠየቀ። ከዚያም በነፃ የምንሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያስተዋውቅ ፖስተር ተመለከተ። “እንዴት ነው መጽሐፍ ቅዱስ የምታስተምሩት?” ሲልም ጠየቀ። ወንድማችን ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር ካሳየው በኋላ ትምህርቱ እንዴት እንደሚሰጥ አስረዳው። ቀጣይ ውይይት ለማድረግ በቀጠሮ ተለያይተዋል።

አንዲት እህታችን ለአንዲት ሴት ድረ ገጻችንን አሳየቻት፤ እንዲሁም ስለምናከናውነው የስብከት ሥራ በአጭሩ አስረዳቻት። በዚህ ጊዜ ሴትየዋ “ሌሎች ምን እንቅስቃሴዎችስ ታደርጋላችሁ?” የሚል ጥያቄ አነሳች። እህታችን በስብሰባ አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የተሰኘውን ቪዲዮ ከፈተችላት። ሴትየዋ ቪዲዮውን በትኩረት ተመለከተች። ከዚያም እንዲህ ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች፦ “ስብሰባችሁ ደስ የሚልና የሚጋብዝ ይመስላል። መጥቼ ማየት እፈልጋለሁ።” በቀጣዩ ሳምንት ሴትየዋ ለሁለት ሰዓታት ገደማ ተጉዛ በስብሰባ ላይ ተገኘች።

የባንኮክ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን፣ ሌሎች ‘ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነውን የአምላክ ሰላም’ እንዲያጣጥሙ የመርዳት አጋጣሚ በማግኘታቸው ተደስተናል።​—ፊልጵስዩስ 4:7