የካቲት 24, 2020
ታይላንድ
በታይላንድ የተካሄደ ልዩ የስብከት ዘመቻ
በ11 አገሮች ከሚገኙ የታይ ቋንቋ ጉባኤዎችና ቡድኖች የተውጣጡ ወንድሞችና እህቶች ከታኅሣሥ 1, 2019 እስከ ጥር 31, 2020 በተካሄደው ልዩ ዘመቻ ላይ ለመካፈል ወደ ታይላንድ ተጉዘው ነበር። ዘመቻው የተካሄደው በታይላንድ የሚኖሩ 4,800 የሚሆኑ የታይ ቋንቋ ተናጋሪ አስፋፊዎች በዋና ከተማው በባንኮክና በአቅራቢያው ለሚኖሩ የታይ ቋንቋ ተናጋሪዎች ለመስበክ የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ ነው። በዘመቻው የተካፈሉት ከ600 የሚበልጡ አስፋፊዎች 34,625 ሰዓታት በአገልግሎት አሳልፈዋል፤ 32,718 ጽሑፎች አበርክተዋል፤ 6,637 ቪዲዮዎች አሳይተዋል እንዲሁም 310 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አስጀምረዋል።
ይህ ዘመቻ ባለፉት ሁለት ዓመታት በታይላንድ ከተደረጉት ዘመቻዎች ሁለተኛው ነው። የታይላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ፕላኮርን ፔስታንዬ የመጀመሪያው ዘመቻ ከታኅሣሥ 2018 እስከ ጥር 2019 ከተካሄደ በኋላ እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፦ “የተጀመሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ብዛትና ዘመቻው በጉባኤዎቹ ላይ ያሳደረው አዎንታዊ ተጽዕኖ ከጠበቅነው በላይ ነው።” የመጀመሪያው ዘመቻ ግሩም ውጤት በማስገኘቱ ቅርንጫፍ ቢሮው ሁለተኛ ዘመቻ እንዲካሄድ ዝግጅት አደረገ።
ለሁለተኛው ዘመቻ ከተለያዩ አገሮች ከመጡት አስፋፊዎች አንዳንዶቹ ተጨማሪ ሰዎችን ስለ ይሖዋ ለማስተማር ሲሉ ቆይታቸውን አራዝመዋል። ከኮሪያ የመጡ አንድ ባልና ሚስት ታይላንድ ውስጥ ለመቆየት ያሰቡት ለአንድ ወር ብቻ ነበር። ሆኖም ፍላጎት ያሳዩ ብዙ ሰዎች በማግኘታቸው ምክንያት ቆይታቸውን በሁለት ሳምንት ለማራዘም ወሰኑ። በዘመቻው ለመካፈል ስትል ሥራዋን ለቃ ከኮሪያ የመጣች ሌላ እህት ደግሞ በታይላንድ ለመኖር ወስናለች።
አስፋፊዎች በዚህ ዘመቻ ወቅት ያደረጉት ጥረት ፍሬያማ ሆኗል። አንዲት እናትና ሴት ልጇ ሲያገለግሉ አንዲትን ሴት በሥራ ቦታዋ አነጋገሯት። በዚህ ወቅት “ልጆች ሊማሯቸው የሚገቡ ስድስት ትምህርቶች” የሚል ርዕስ ያለውን ቁጥር 2, 2019 ንቁ! መጽሔት አበረከቱላት። በቀጣዩ ጊዜ ሊያነጋግሯት ሲመጡ ሴትየዋ የሰጧትን ንቁ! መጽሔት እያውለበለበች በደስታ ተቀበለቻቸው። ሴትየዋ “የሚገርም ሐሳብ የያዘ ጽሑፍ ነው! እባካችሁ ይበልጥ ማወቅ እንድችል እርዱኝ” አለቻቸው። አስፋፊዎቹ ሴትየዋን በሳምንት አንድ ቀን በምሳ እረፍቷ ወቅት ለማስጠናት ዝግጅት አደረጉ። በተጨማሪም JW ላይብረሪ የተባለውን አፕሊኬሽን እንድታወርድ ረዷት። በአሁኑ ወቅት ሴትየዋ በሳምንት ሁለቴ ታጠናለች፤ እንዲሁም እንደ ነጭ ሰሌዳ አኒሜሽኖች ያሉ ቪዲዮዎችን ለልጆቿ ማሳየት ያስደስታታል።
አንዲት ሌላ አስፋፊ ያገኘቻት ሴት ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው አለባበስና ወዳጃዊ ስሜት በጣም ማረካት። ሴትየዋ ጓደኛ ፍለጋ ወደተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች ብትሄድም እንዳልተሳካላት ገለጸች። አስፋፊዋ በዚያው ቀን በሚደረግ የጉባኤ ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ሴትየዋን ጋበዘቻት። ሴትየዋም በስብሰባው ላይ የተገኘች ሲሆን የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸውን ወንድሞችና እህቶች በመተዋወቋ ተደሰተች። ከአምላክ የተላከ ምሥራች! በተባለው ብሮሹር አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች፤ እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ በቀጣይነት ለመገኘት ፍላጎት አሳይታለች።
አንዲት እህት ከባንኮክ አውራጃዎች አንዱ በሆነው በባንግ ና በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ አንዲት ሴት አገኘች። ሴትየዋ ቤተ ክርስቲያን ሄዳ የምታውቅ ቢሆንም የራሷ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሌላት ተናገረች። ከዚያም እህት JW ላይብረሪን እና አዲስ ዓለም ትርጉምን አወረደችላት። አስፋፊዎቹ ተመላልሶ መጠየቅ ሲያደርጉላት ሴትየዋ በቅርቡ በተጫነላት አፕሊኬሽን ተጠቅማ መጽሐፍ ቅዱስን እያነበበች እንደሆነ ነገረቻቸው። ከዚያም እህቶች ምሥራች በተባለው ብሮሹር የጀርባ ገጽ ላይ ያሉትን ጥያቄዎች አንድ በአንድ አነበቡላት። ሴትየዋም የሁሉንም ጥያቄዎች መልስ ማወቅ እንደምትፈልግ ነገረቻቸው። በዚህ መልኩ እህቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀመሯት፤ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ከምትኖር እህት ጋር እያጠናች ነው። ሴትየዋ በሕይወቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ መንፈሳዊ ነገሮች በራሷ ምርምር ማድረግ በመቻሏ በጥናቷ በጣም እንደተደሰተች ገልጻለች።
አንዲት እህት ከቤት ወደ ቤት ስታገለግል አንድ ባልና ሚስት አገኘች፤ ባልየው የታይላንድ፣ ሚስትየዋ ደግሞ የላኦ ተወላጅ ናቸው። እህት በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለምን ነገር እንደሆነ ጠየቀቻቸው። እነሱም “ለቤተሰባችን” ብለው መለሱላት። እህትም ከአምላክ የተላከ ምሥራች! ከተባለው ብሮሹር ላይ ስለ ቤተሰብ የሚናገረውን ሐሳብ አካፈለቻቸው። ባልና ሚስቱም ምክሩ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማሙ። ብዙም ሳይቆይ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኙ። በስብሰባው ላይ የተመለከቱት ሞቅ ያለ ወዳጃዊ መንፈስ በጣም ስላስደሰታቸው በቀጣይነት በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ወስነዋል።
በታይላንድ በተካሄደው ዘመቻ ላይ የተገኙት እነዚህና ሌሎችም በርካታ ተሞክሮዎች የይሖዋ ሕዝቦች በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ‘የጌታ ሥራ እንደበዛላቸው’ ያሳያሉ።—1 ቆሮንቶስ 15:58