በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በታይላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ እድሳት የተካፈሉ የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች። ውስጠኛው ፎቶግራፍ ላይኛው፦ የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች የነበሩ አሁን በታይላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ እያገለገሉ ያሉ ወንድሞች። ውስጠኛው ፎቶግራፍ የታችኛው፦ አንዲት የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኛ (መሃል ላይ ያለችው) በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ስትካፈል

ሰኔ 28, 2023
ታይላንድ

የታይላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ መቋረጡ ያልተጠበቁ በረከቶችን አስገኘ

የታይላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ መቋረጡ ያልተጠበቁ በረከቶችን አስገኘ

በ2019 በታይላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ የግንባታና የእድሳት ፕሮጀክት ተጀምሮ ነበር፤ በዚህ ፕሮጀክት ላይ የአካባቢው ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ፈቃደኛ ሠራተኞች እየተሳተፉ ነበር። ሆኖም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰት ፕሮጀክቱ ላይ ከተመደቡት 50 ዓለም አቀፍ ፈቃደኛ ሠራተኞች መካከል 42ቱ ወደ አገራቸው ተመለሱ። የተጣሉት ገደቦች ሲነሱ ግን ሥራው ቀጠለ። በመሆኑም በአካባቢው ያሉ ተጨማሪ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሥልጠና አግኝተው ፕሮጀክቱን በማጠናቀቁ ሥራ እንዲያግዙ ተጋበዙ። ሚያዝያ 30, 2023 የሥራው የመጨረሻ ምዕራፍ ተጠናቀቀ።

በአገሪቱ ካሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች መካከል ወንድም ሴትሃሳት ታዋንሲሪኩል እና ባለቤቱ ዋራፖርን ይገኙበታል። እነዚህ ባልና ሚስት፣ በቂ ልምድ የሌላቸው መሆኑ መጀመሪያ ላይ አሳስቧቸው ነበር። ወንድም ሴትሃሳት “እዚያ ከደረስን በኋላ ልዩ ሥልጠና ተሰጠን” ብሏል።

በዚህ ፕሮጀክት የተካፈሉ በአካባቢው ያሉ በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች፣ በሥራው መካፈላቸው ያስገኘላቸውን ከፍተኛ ደስታና እርካታ ሲያዩ በሌሎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች ለመካፈል ተነሳስተዋል። አሁን አንዳንዶቹ በመላው የታይላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ክልል ውስጥ በሚካሄዱ የግንባታ ፕሮጀክቶች እየተካፈሉ ነው። አንዲት እህት በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት እየተማረች ነው። ሌሎቹ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በቤቴል እያገለገሉ ይገኛሉ። ከእነዚህ አዳዲስ የቤቴል ቤተሰብ አባላት መካከል አንዱ የሆነው ወንድም ራፒፓት ዎራዴትሳኩል እንዲህ ብሏል፦ “በግንባታ ፕሮጀክቱ ላይ የይሖዋን እርዳታ መመልከቴ፣ በቤቴል እንዳገለግል የቀረበልኝን ግብዣ ለመቀበል ድፍረት ሰጥቶኛል። በዚህ አዲስ ምድብ ይሖዋ እንደሚረዳኝ እርግጠኛ ነኝ።”

የታደሰው የታይላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ከላይ ሲታይ። ውስጠኛው ፎቶግራፍ የላይኛው፦ ወደ ቢሮ የተቀየረው ሕንፃ ከውስጥ ሲታይ። ውስጠኛው ፎቶግራፍ መካከለኛው፦ አዲስ የተገነባው የጥገና ሕንፃና መጋዘን። ውስጠኛው ፎቶግራፍ የታችኛው፦ አዲስ የተገነባው የመኪና ማቆሚያ ቦታ

በታይላንድ ቅርንጫፍ ቢሮ የተከናወነው የግንባታና የእድሳት ሥራ የመኖሪያና የቢሮ ሕንፃዎች እድሳትን፣ አዲስ የጥገና ሕንፃና የመጋዘን ግንባታን እንዲሁም አዲስ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ግንባታን ያካትታል። በተጨማሪም ለቤቴል ቤተሰብ አባላት ተጨማሪ የመኖሪያ ቦታ ለማዘጋጀት ሲባል በቅርንጫፍ ቢሮው አቅራቢያ በሚገኝ አፓርትመንት ላይ ስድስት መኖሪያ ቤቶች ተገዝተው ማስተካከያ ተደርጎባቸዋል።

በታይላንድ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለይሖዋ አገልግሎት ራሳቸውን በፈቃደኝነት በማቅረባቸው በጣም ደስተኞች ነን፤ እንዲህ በማድረጋቸውም በመዝሙር 34:8 ላይ የሚገኙትን “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም” የሚሉትን ቃላት እውነተኝነት በገዛ ሕይወታቸው እየተመለከቱ ነው።