በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሐምሌ 5, 2019
ታይዋን

የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በቻይንኛ ወጣ

የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም በቻይንኛ ወጣ

ሐምሌ 5, 2019 በታውዩወን ሲቲ፣ ታይዋን በተካሄደው የክልል ስብሰባ ላይ የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በቻይንኛ መውጣቱ ተገለጸ። መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱ የተገለጸው የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ኬነዝ ኩክ በናሽናል ታይዋን ስፖርት ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ባቀረበው ንግግር ላይ ነው። በአራት ሌሎች የክልል ስብሰባዎች ላይ ንግግሩን በቪዲዮ ይከታተሉ የነበሩ ተሰብሳቢዎችን ጨምሮ በድምሩ 12,610 ሰዎች ይህን ልዩ ክንውን ታድመዋል።

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ለመጀመሪያ ጊዜ በቻይንኛ የወጣው በ1995 ሲሆን የወጣውም በሁለት እትሞች ነው፤ አንደኛው እትም የተዘጋጀው በሆንግ ኮንግ እና በታይዋን በስፋት በሚሠራበት በጥንታዊው አጻጻፍ ሲሆን አንደኛው ደግሞ የተዘጋጀው በማሌዥያ፣ በሲንጋፖርና በቻይና በስፋት በሚሠራበት ቀለል ባለው የአጻጻፍ ስልት ነው። ሙሉው አዲስ ዓለም ትርጉም በ2001 በቻይንኛ ወጣ፤ በዚህ ወቅትም ቢሆን የወጣው በሁለት እትሞች ይኸውም በጥንታዊው አጻጻፍና ቀለል ባለው አጻጻፍ ነው። በ2004 ደግሞ ቀለል ያለውን የቻይንኛ አጻጻፍ ከፒንዪን (በላቲን ፊደላት የተጻፈ አነባበቡን የሚጠቁም ጽሑፍ) ጋር የያዘ ሦስተኛ እትም ወጣ።

የተሻሻለው አዲስ ዓለም ትርጉምም የወጣው በሦስት እትሞች ነው። በጥንታዊውና ቀለል ባለው አጻጻፍ የተዘጋጁትን መጽሐፍ ቅዱሶች በሕትመትም ሆነ በዲጂታል ፎርማት ማግኘት ይቻላል፤ ፒንዪን የያዘው እትም የሚገኘው ግን የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት ላይ ብቻ ነው።

በዓለም ዙሪያ ቻይንኛ ማንዳሪን የሚናገሩ ከ1.1 ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች አሉ፤ ይህም ከሌሎች ቋንቋዎች ሁሉ የበለጠ ቁጥር ነው። ቻይንኛ ማንዳሪን ከሚናገሩ ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች የቻይንኛ ቀበሌኛዎች የሚናገሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም የቻይንኛ ጽሑፍን ማንበብ ይችላሉ። አሁን በዚህ ሰፊ መስክ የሚያገለግሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ብዙ ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁና ስለ ቃሉ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት የተሻሻለውን አዲስ ዓለም ትርጉም መጠቀም ይችላሉ።—1 ጢሞቴዎስ 2:4