በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ (በግራ በኩል ሁለተኛው) ከእናቱ ከፋሪዛ፣ ከወንድሙ ከራቭሻንና ከአባቱ ከባቲር ጋር፤ በ2016 በኪርጊስታን የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ ሲጎበኙ

ጥቅምት 27, 2020
ታጂኪስታን

በታጂኪስታን ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ከፍርድ በፊት ታስሮ ይገኛል፤ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስር ሊፈረድበት ይችላል

በታጂኪስታን ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ከፍርድ በፊት ታስሮ ይገኛል፤ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስር ሊፈረድበት ይችላል

የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን

የታጂኪስታን ወታደራዊ ፍርድ ቤት በወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ላይ የቀረበውን ክስ ተመልክቶ በቅርቡ a ውሳኔውን ያሳውቃል። ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ በሕሊናው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከሁለት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት ሊፈረድበት ይችላል። ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ከጥቅምት 1, 2020 ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛል።

አጭር መግለጫ

ሩስታምጆን ኖሮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1998 (ዱሻንበ)

  • ግለ ታሪክ፦ ቤቶችንና የቤት ዕቃዎችን በማደስ ሥራ ላይ ተሠማርቶ ራሱን ያስተዳድር፣ ቤተሰቡንም ይረዳ ነበር። እግር ኳስ መጫወት ያስደስተዋል

  • በ2016 በ17 ዓመቱ ተጠመቀ። ከቤተሰቡ ጋር በሩሲያኛ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ የነበረ ቢሆንም ከተጠመቀ ከሁለት ዓመት በኋላ የታጂክ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ለመርዳት ሲል በታጂክ ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ተዛወረ

የክሱ ሂደት

በ2016 ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ወታደራዊ ምልመላ ወደሚያካሂደው ቢሮ በፈቃዱ ሄዶ ስለ ገለልተኝነት አቋሙ ካስረዳ በኋላ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት መስጠት እንዲፈቀድለት ጠየቀ። በቀጣዩ ዓመትም ተመሳሳይ ነገር አደረገ። በምልመላ ቢሮው የሚሠራው ባለሥልጣን የወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭን አቋም ያከበረለት ሲሆን በሰጠው ማብራሪያም ተገረመ። ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ለብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት አልተጠራም።

ይሁን እንጂ መስከረም 24, 2020 ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ወደ አውራጃው የውትድርና ምልመላ ቢሮ ተጠራ። በዚያ የሚሠሩት ባለሥልጣናት ለሦስት ሰዓት ያህል በጥያቄ ሲያፋጥጡት ከቆዩ በኋላ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ጤንነቱ እንደሚፈቅድለት ገለጹ። ከዚያም ባለሥልጣናቱ የጤና ምርመራ እንዲያደርግ ለማስገደድ ሞከሩ። የወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ አባት ሁኔታውን ሲመለከት ባለሥልጣናቱ የልጁን ጉዳይ ወደ አቃቤ ሕግ ቢሮ እንዲመሩት ጠየቀ።

ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭና አባቱ ጥቅምት 1 ወደ አቃቤ ሕግ ቢሮ ሄዱ። አቃቤ ሕጉም አንድ የአውራጃ ፖሊስ ወደ አውራጃው የውትድርና ምልመላ ቢሮ እንዲወስዳቸው አደረገ። እዚያ ሲደርሱ የወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ አባት እንዳይገባ ተከለከለ። ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ግን ለሁለት ቀን ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ተደረገ። በወቅቱ የወንጀል ክስ አልተመሠረተበትም፤ ፍርድ ቤትም አልቀረበም። በማረፊያ ቤት በነበረበት ወቅት ፖሊሶቹ ከጠበቃው ጋር እንዲነጋገር አልፈቀዱለትም።

ጥቅምት 3 ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ቤተሰቦቹ ከሚገኙበት ከዱሻንበ 300 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኘው በኩጃንድ ከተማ ወዳለ ወታደራዊ ካምፕ ተወሰደ። በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ኩጃንድ ውስጥ ወደሚገኙ የተለያዩ ወታደራዊ ካምፖች ተወስዷል።

ጥቅምት 6 ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ቤተሰቦቹ ጋ መደወልና ጠበቃውን አግኝቶ ማነጋገር ተፈቀደለት። ይሁን እንጂ ጥቅምት 17 አንድ የታጂኪስታን ወታደራዊ ፍርድ ቤት ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ከፍርድ በፊት እንዲታሰር ወሰነ። አቃቤ ሕጉ የምርመራውን ሂደት እስኪያጠናቅቅና ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን እስኪያስተላልፍ ድረስ ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ በእስር ይቆያል። ወንድማችን ከወታደራዊ አገልግሎት ለማምለጥ ሲል የውሸት የሕክምና ሰነድ አቅርቧል የሚል ክስ ተመሥርቶበታል።

ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ እስር ቤት ውስጥ ቢሆንም በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት ስላለው ተስፋ አልቆረጠም። ይሖዋ ይህን ፈተና ለመቋቋም የሚያስችለው እምነትና ድፍረት እንዲያዳብር ስለረዳው አመስጋኝ ነው። በተጨማሪም በ2013 ያጋጠመው አንድ ያልተጠበቀ ፈተና እንደረዳው ይሰማዋል። በዚያ ዓመት ፖሊሶች ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭና ታናሽ ወንድሙ ራቭሻን ወደሚማሩበት ትምህርት ቤት በመሄድ ለሕክምና ምርመራ ወደ ወታደራዊ ምልመላ ቢሮ አስገድደው ወስደዋቸው ነበር። በወቅቱ ሩስታምጆን ገና 15 ዓመቱ ስለነበር የውትድርና አገልግሎት ለመስጠት ዕድሜው አልደረሰም። በዚያን ጊዜ ያልተጠመቀ አስፋፊ ነበር። ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ፣ የልጆቹ አባት የሆነው ወንድም ባቲር በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ልጆቹ ስለ ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው ጥብቅና እንዲቆሙ ለማሠልጠን ጊዜ መደበ። ወንድም ባቲር እንደ ምልመላ ባለሥልጣን በመሆን ልጆቹ ለእምነታቸው ጥብቅና መቆም የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ያለማምዳቸው ነበር።

ሩስታምጆን እንዲህ ብሏል፦ “በቤተሰብ አምልኮ ወቅት እንዲህ ያለ ልምምድ ማድረግ ከመጀመራችን በፊት ለእምነቴ ጥብቅና ለመቆም ዝግጁ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር። ሆኖም በልምምዱ ወቅት ሁኔታው ምን ያህል ሊያስፈራኝና ሊያስጨንቀኝ እንደሚችል ስመለከት ተገረምኩ። ያደረግነው ልምምድ ስለ እምነቴ የበለጠ መጸለይና ስለ ገለልተኝነት አቋም ተጨማሪ ምርምር ማድረግ እንዳለብኝ አስገንዝቦኛል። ቀስ በቀስ ፍርሃቴ እየጠፋ ሄደ። በ2016 መጀመሪያ አካባቢ ሕይወቴን ለይሖዋ ወሰንኩና ተጠመቅኩ።”

ሩስታምጆን በእምነታቸው ምክንያት ታስረው ከነበሩ በዕድሜ የሚበልጡት የጎለመሱ ወንድሞች ጋር ጊዜ ማሳለፉም አበረታቶታል። እንዲህ ብሏል፦ “የገለልተኝነት አቋሜ ምን ሊያስከትልብኝ እንደሚችል በደንብ ገብቶኛል። እንድታሰር ከተፈረደብኝ ‘በአዲስ ክልል’ ውስጥ የይሖዋን ስም የማስቀደስ መብት እንዳገኘሁ አድርጌ እቆጥረዋለሁ።”

የሩስታምጆን አባት እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋን ፈቃድ የማድረግ አጋጣሚ ማግኘታችንንና እሱ ሊጠቀምብን መቻሉን ቤተሰባችን እንደ ታላቅ ክብር ይቆጥረዋል። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላሳዩን ፍቅር፣ ለጸሎታቸውና ለሰጡን ስሜታዊም ሆነ መንፈሳዊ ድጋፍ በጣም አመስጋኞች ነን። ከመጠን በላይ አንጨነቅም። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል በገባልን መሠረት የአምላክ ሰላም ልባችንን ሞልቶታል!”—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

a ፍርድ ቤቱ ብይን የሚያስተላልፍበትን ቀን አስቀድሞ የማያሳውቅበት ጊዜ አለ