በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ታጂኪስታን ውስጥ ከእስር ከመለቀቁ በፊት

ጥቅምት 12, 2021
ታጂኪስታን

ከእስር የተፈታው ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ምሳሌ የሚሆን ምግባር በማሳየቱ ተመሰገነ

ከእስር የተፈታው ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ ምሳሌ የሚሆን ምግባር በማሳየቱ ተመሰገነ

ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ በታጂኪስታን የሚኖረው ወንድም ሩስታምጆን ኖሮቭ (አሁን 22 ዓመቱ ነው) የተፈረደበትን ጊዜ ሳይጨርስ መስከረም 21, 2021 ከእስር ተለቅቋል፤ ይህ የሆነው በወሩ መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ በሆነው የምሕረት ሕግ ምክንያት ነው። ሩስታምጆን በተለያዩ ማረፊያ ቤቶች ውስጥ በድምሩ ሦስት ወር ቆይቷል። ከዚያም የሦስት ዓመት ተኩል እስራት ተፈርዶበት ግንቦት 10, 2021 በያቫን ወደሚገኝ ማረሚያ ቤት ተዛወረ። ማረፊያ ቤት ውስጥ፣ ችሎት ፊት በቀረበበት ወቅት እንዲሁም ማረሚያ ቤት ውስጥ ባሳለፈው ጊዜ ሁሉ ያሳየው መልካም ምግባርና የዓላማ ጽናት ሌሎችን አስደንቋል።

በአንድ ወቅት ሩስታምጆን ችሎት ፊት ቀርቦ እያለ አንድ ኮሎኔል መጥቶ ጨበጠው። ኮሎኔሉ፣ በቆራጥነቱና በድፍረቱ ሩስታምጆንን ምን ያህል እንደሚያደንቀው ገለጸለት። “አማኝ የሆነ ሰው ሁሉ እንደ አንተ መሆን አለበት” አለው። አክሎም እንዲህ አለው፦ “እስቲ አስበው፤ ከዓመታት በኋላ በታጂኪስታን አማራጭ የሲቪል አገልግሎትን የሚፈቅድ ሕግ ሲወጣ ይህ የዜጎች መብት እንዲከበር መሥዋዕትነት ከከፈሉ ሰዎች መካከል የአንተም ስም ይጠቀሳል።”

ሩስታምጆን ማረሚያ ቤት በነበረበት ጊዜም ግሩም ምሥክርነት ሰጥቷል። ምሳሌ የሚሆን ምግባር በማሳየቱ የማረሚያ ቤቱ ባለሥልጣናት የአውሮፓ ሕብረት ባዘጋጀው አንድ ልዩ ሥልጠና ላይ እንዲካፈል ጋበዙት፤ ይህ ሥልጠና እስረኞች ከተለቀቁ በኋላ ሥራ ለማግኘት እንዲረዳቸው ታስቦ የተዘጋጀ ኮርስ ነው። ሥልጠናውን ካጠናቀቀ በኋላ የማረሚያ ቤቱ ባለሥልጣናት ለሩስታምጆን የምሥክር ወረቀትና ላሳየው ትጋት አድናቆታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ሰጡት። ባለሥልጣናቱ ‘እንዲህ ዓይነት ግሩም ባሕርይ ሊኖርህ የቻለው የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግህ ነው’ እንዳሉት ሩስታምጆን ተናግሯል።

ሩስታምጆን ማረሚያ ቤት ሳለ የምሕረት ሕጉ ለእሱ የሚሠራ መሆኑን ተጠራጥሮ ነበር። ሆኖም ሌሎቹ እስረኞች፣ ሩስታምጆን እስር ቤት ውስጥ ያተረፈውን መልካም ስም በመጥቀስ እንደሚፈታ እርግጠኛ መሆናቸውን ገልጸውለታል። ብዙ የማረሚያ ቤቱ ባለሥልጣናትም አበረታትተውታል።

በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት የታሰሩና በአቋማቸው የጸኑ እንደ ሩስታምጆን ያሉ ታማኝ ወጣቶች ‘ብርሃናቸው በሰው ፊት እንዲበራ’ እያደረጉ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ የሚያከናውኑት “መልካም ሥራ” ለይሖዋ አምላክ ክብርና ውዳሴ ያመጣል።—ማቴዎስ 5:16