በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ጆቪዶን ቦቦጆኖቭ

ኅዳር 18, 2020
ታጂኪስታን

ወንድም ጆቪዶን ቦቦጆኖቭ በታጂኪስታን ፕሬዚዳንት ምሕረት ተደርጎለት ከእስር ተፈታ

ወንድም ጆቪዶን ቦቦጆኖቭ በታጂኪስታን ፕሬዚዳንት ምሕረት ተደርጎለት ከእስር ተፈታ

ወንድም ጆቪዶን ቦቦጆኖቭ ኅዳር 1, 2020 ከእስር ከተፈታ በኋላ “ይሖዋ በእምነቴ ጸንቼ እንድቀጥል ረድቶኛል” በማለት ተናግሯል። ይህ ከመሆኑ ከአንድ ቀን በፊት የታጂኪስታን ፕሬዚዳንት ለጆቪዶንና ለሌሎች 377 እስረኞች ምሕረት አድርገዋል። ጆቪዶን በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከተፈረደበት የሁለት ዓመት እስራት ውስጥ ዘጠኝ ወሩን አጠናቆ ወጥቷል።

ጥቅምት 4, 2019 ወታደሮች በወቅቱ 19 ዓመቱ የነበረውን ጆቪዶንን ከቤቱ አስገድደው ከወሰዱት በኋላ ምዝገባ በሚደረግበት ቢሮ ውስጥ እንዲቆይ አደረጉት። በቀጣዮቹ ወራት ወደተለያዩ ወታደራዊ ተቋማት ተዘዋውሯል። በእያንዳንዱ ጊዜያዊ ማቆያ ተቋም ውስጥ በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ያልሆነበትን ምክንያት እንዲያብራራ ጥያቄ ይቀርብለት ነበር። “ብዙ አዛዦችና ወታደሮች ምክንያታዊ ያልሆኑ ጥያቄዎችን ያቀርቡልኝ ነበር፤ የሁሉም ፍላጎት ሃይማኖቴን እንድተው ማድረግ ነበር” በማለት ጆቪዶን ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በቁጣ እንድገነፍል ለማድረግ ሆን ብለው እነዚህን ጥያቄዎች ይጠይቁኛል። ሌሊት ላይ ከእንቅልፌ ቀስቅሰው እነዚያኑ ጥያቄዎች ደጋግመው የሚጠይቁኝ ጊዜ አለ፤ በሠራዊቱ ውስጥ የማላገለግለው ለምን እንደሆነ እንድነግራቸው ይፈልጋሉ።

“ሆኖም ጸሎት በጣም ጠቅሞኛል። በወታደራዊ ማቆያ ተቋም ውስጥ ሌት ተቀን በእንባ ጭምር ወደ ይሖዋ በመጸለይ ተስፋ እንዳልቆርጥ፣ እሱን እንዳላሳዝነውና በቁጣ ገንፍዬ እንዳልናገር እንዲረዳኝ እለምነው ነበር።

“ይሖዋ እጄን ጥብቅ አድርጎ ይዞኝ ነበር። . . . የብቸኝነት ስሜት ሲሰማኝ ውስጤ ቢረበሽም ይሖዋ በፍጥረት ሥራዎቹ ተጠቅሞ አበርትቶኛል። በየዕለቱ ማለዳ ላይ ከእንቅልፌ ስነሳ ወፎች ሲያዜሙ እሰማለሁ። ምሽት ላይ ደግሞ ጨረቃንና ከዋክብትን እመለከታለሁ። ከይሖዋ ያገኘኋቸው እነዚህ ስጦታዎች ደስተኛ እንድሆንና እንድበረታ ረድተውኛል።”

ሚያዝያ 2, 2020 ጆቪዶን ጥፋተኛ ነው ተብሎ የተፈረደበት ሲሆን ከጊዜያዊ ማቆያ ተቋም ወደ እስር ቤት ተዛወረ። እስር ቤት ውስጥ ደብዳቤ መቀበል አይፈቀድለትም ነበር። ሆኖም ወንድሞችና እህቶች ምግብ ይዘውለት ሲሄዱ ዕቃ በገዛዙበት ከረጢት ላይ የዕለቱን ጥቅስ ይጽፉለታል። “ይህ የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማኝና ወዳጆቼ ምን ያህል አሳቢ እንደሆኑ እንድገነዘብ አድርጎኛል” በማለት ጆቪዶን ተናግሯል።

በተጨማሪም ጆቪዶን እንደ ሮም 8:37-39 ያሉ አበረታች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማስታወስ በመቻሉ ደስተኛ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “እስር ቤት ሳለሁ እነዚህ ቃላት ምን ያህል እውነት እንደሆኑ አይቻለሁ። የትኛውም ፈተና ከይሖዋ ፍቅር ሊለየኝ አልቻለም። ይሖዋ በእምነቴ ጸንቼ እንድቀጥል ረድቶኛል።”

የጆቪዶን ተሞክሮ ወላጆቹን አበረታቷቸዋል። አባቱ አብዱጃሞል እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ይሖዋ መጸለያችንና ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ የተወጣውን ልጃችንን ምሳሌ ማየታችን እምነታችንን አጠናክሮታል። በዓለም ዙሪያ ያሉ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ድጋፍ አልተለየንም። በጸሎታቸው ስላሰቡን ከልብ እናመሰግናለን። ይሖዋ እንዲህ ያሉ አፍቃሪና አሳቢ ወዳጆች ስለሰጠን በጣም አመስጋኞች ነን።”

በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ሁላችንም “እንደ እሳት [ያሉ] ከባድ ፈተናዎች” እንደሚያጋጥሙን እንጠብቃለን። (1 ጴጥሮስ 4:12) ከዚህ አንጻር ጆቪዶን ሐሳቡን ሲደመድም እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ነፃ ስለሆንኩ ይህን ነፃነቴን ስለ ይሖዋ ያለኝን እውቀት ለማሳደግ እንዲሁም ወደፊት ለሚያጋጥሙኝ ፈተናዎች ራሴን ለማዘጋጀት ልጠቀምበት አስቤያለሁ። እስካሁን ከባድ ፈተና አጋጥሟችሁ የማያውቅ ከሆነ ነፃነታችሁን የአምላክን ቃልና ድርጅቱ ያዘጋጃቸውን ጽሑፎች በማንበብ ስለ ይሖዋ ያላችሁን እውቀት ለማሳደግ ልትጠቀሙበት ይገባል።”