በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ ከእስር ቤት በወጣበት ወቅት ወንድሞችና እህቶች ሲቀበሉት

ግንቦት 16, 2023
ታጂኪስታን

የሰባ ሁለት ዓመቱ ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ በታጂኪስታን ከእስር ተለቀቀ

የሰባ ሁለት ዓመቱ ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ በታጂኪስታን ከእስር ተለቀቀ

ግንቦት 16, 2023 ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ በታጂኪስታን ከሚገኝ እስር ቤት ተለቀቀ። በእምነቱ ምክንያት ለአራት ዓመታት ከታሰረ በኋላ ወደ ቤቱ ተመልሷል።

ወንድም ሻሚል በ2019 ከመታሰሩ በፊትም ቢሆን ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የልብ ሕመምና ሌሎች የጤና እክሎች ነበሩበት። እንዲህ ካሉ የጤና ችግሮች ጋር እየታገለ ቢሆንም እንኳ እስር ቤት እያለ ተገቢውን የጤና ክትትል ማግኘት አልቻለም። በዚህም የተነሳ ጤንነቱ እያሽቆለቆለ ሄደ፤ ይባስ ብሎም እግሩ ላይ ያለው ቁስል ተመረዘ።

ወንድም ሻሚል ወህኒ ቤት ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል፤ በዚያ ላይ ደግሞ ከባድ ሥቃይ የሚያስከትል ሕመም ነበረበት፤ ያም ቢሆን በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙ ጥቅሶች ላይ ትኩረት በማድረግ አዎንታዊ አመለካከት ይዞ መቆየት ችሏል።

የሻሚል ወዳጆች “ሻሚል እንወድሃለን!” የሚል ጽሑፍ ይዘው ከእስር ቤቱ ውጭ ሲቀበሉት

ወንድም ሻሚል ብዙውን ጊዜ በጸሎቱ ላይ በመዝሙር 141:8 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ያካትታል፤ ጥቅሱ “ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ ዓይኖቼ ግን ወደ አንተ ይመለከታሉ። አንተን መጠጊያዬ አድርጌአለሁ” ይላል። በተጨማሪም የተጎሳቆሉ ሰዎች ስም በምሳሌያዊ ሁኔታ በይሖዋ ‘እጅ መዳፍ ላይ እንደተቀረጸ’ የሚናገረው በኢሳይያስ 49:13, 16 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በጣም አጽናንቶታል። ይህ ጥቅስ ወንድም ሻሚል እስር ቤት ውስጥ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ እንደማይረሳው እርግጠኛ እንዲሆን ረድቶታል።

ከይሖዋ ቃል ማጽናኛ ስላገኘ ደስታውን ጠብቆ መቀጠል ከዚያም አልፎ ሌሎችን ማበረታታት ችሏል። ወንድም ሻሚል እስር ቤት በነበረበት ወቅት አዘውትሮ ይጠይቀው የነበረ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ለመጀመሪያ ጊዜ ስደውልለት በሐዘን የተዋጠና የተደቆሰ ሰው ድምፅ እንደምሰማ ጠብቄ ነበር። እሱ ግን መንፈሰ ጠንካራ ነው። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ አዎንታዊ አመለካከት ነበረው፤ እንዲያውም እኛን ያበረታታን ነበር።”

ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:25 “ይሖዋ በእሱ ተስፋ ለሚያደርግ፣ እሱንም ዘወትር ለሚሻ ሰው ጥሩ ነው” ይላል። ይሖዋ ለወንድም ሻሚልና በታጂኪስታን ለሚገኙ መከራን በደስታ እየተቋቋሙ የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምንጊዜም “ጥሩ” እንደሚሆንላቸው እንተማመናለን፤ በጸሎታችንም እንስባቸዋለን።