በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የካቲት 3, 2022
ታጂኪስታን

የተ.መ.ድ. ኮሚቴ በታጂኪስታን የሚኖረው ወንድም ቴሪ አሜጅሮ መብቱ እንደተጣሰ ገለጸ

የተ.መ.ድ. ኮሚቴ በታጂኪስታን የሚኖረው ወንድም ቴሪ አሜጅሮ መብቱ እንደተጣሰ ገለጸ

ታኅሣሥ 14, 2021 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ፣ የታጂኪስታን መንግሥት ወንድም ቴሪ አሜጅሮን በማሰርና ወደ ካዛክስታን እንዲመለስ በማስገደድ ሰብዓዊ መብቱን እንደጣሰ ገለጸ።

ኮሚቴው፣ እስራቱ ‘ተገቢ እንዳልሆነ’ እንዲሁም የተ.መ.ድ. የሲቪልና ፖለቲካዊ ነፃነት መብቶች ቃል ኪዳንን እንደሚጥስ ገልጿል። በተጨማሪም ኮሚቴው፣ ቴሪ ወደ ታጂኪስታን መመለስ ከፈለገ መንግሥት ሊያግደው እንደማይችል ተናግሯል። አሁን የታጂኪስታን ባለሥልጣናት “ወደፊት ተመሳሳይ የመብት ጥሰት እንዳይከሰት አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ የመውሰድ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።”

የታጂኪስታን ባለሥልጣናት ጥቅምት 4, 2018 የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ እያደረጉ የነበሩበትን ቤት ወረሩ። ባለሥልጣናቱ ቴሪን በቁጥጥር ሥር ካዋሉት በኋላ በታጂኪስታን መንግሥት የብሔራዊ ደህንነት ዋና ቢሮ ወስደው ምርመራ አደረጉበት። ጥቅምት 16, 2018 አንድ ዳኛ፣ ቴሪ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ወደ አገሪቱ እንደገባ በመግለጽ በሐሰት ፈረዱበት። ቴሪ የሩሲያ ዜጋ ሲሆን የሚሠራው በታጂኪስታን ነበር።

ዳኛው በቴሪ ላይ የገንዘብ መቀጮ የጣሉበት ከመሆኑም ሌላ ከአገሪቱ እንዲባረር አዘዙ።

ቴሪ እንዲህ ብሏል፦ “የተ.መ.ድ. ኮሚቴው ውሳኔ በታጂኪስታን ያለውን የሃይማኖት ነፃነት እንደሚያሻሽለውና ወንድሞቻችን በሰላም ይሖዋን ማምለክ እንዲችሉ እንደሚረዳቸው ተስፋ አደርጋለሁ።”

በአሁኑ ወቅት ታጂኪስታን ውስጥ በእምነቱ ምክንያት የታሰረ አንድ ወንድም አለ።

ይሖዋ ፈተናን በጽናት እየተቋቋሙ ላሉ ወንድሞቻችን ዘላቂ ሰላም እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች ነን።—ኢሳይያስ 26:3