በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥቅምት 13, 2022
ታጂኪስታን

የተ.መ.ድ. የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ፣ ታጂኪስታን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የጣለችው እገዳ ሕገ ወጥ ነው አለ

የተ.መ.ድ. የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ፣ ታጂኪስታን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የጣለችው እገዳ ሕገ ወጥ ነው አለ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ፣ በታጂኪስታን የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተፈጸመውን አድሏዊ አያያዝ በተመለከተ መስከረም 7, 2022 ትልቅ ውሳኔ አስተላልፏል። የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴው፣ የአዲርኻዬቭን እና የታጂኪስታንን መንግሥት የክስ መዝገብ ተመልክቶ ሐምሌ 7, 2022 ለይሖዋ ምሥክሮች ፈርዷል። ይህ ውሳኔ ታጂኪስታን ለይሖዋ ምሥክሮች እውቅና ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኗን እንዲሁም ይህን ተከትሎ በእንቅስቃሴዎቻቸው ላይ ለጣለችው እገዳ እልባት የሚሰጥ ነው።

የይሖዋ ምሥክሮች ታጂኪስታን ውስጥ አምልኳቸውን ማካሄድ ከጀመሩ ከ50 ዓመት በላይ አስቆጥረዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ማኅበር በ1994 ሕጋዊ እውቅና ተሰጥቶት ተመዘገበ። ይሁንና ጥቅምት 11, 2007 የታጂኪስታን የባሕል ሚኒስቴር ምዝገባውን ሰርዞ በይሖዋ ምሥክሮች አምልኮ ላይ እገዳ ጣለ። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት አገልግሎት፣ በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውና እውነተኛ ሃይማኖት እንዳላቸው መናገራቸው በታጂኪስታን መንግሥት አመለካከት መሠረት ጽንፈኛ ተብሎ የሚያስፈርጅ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ማኅበርን እንደገና ለማስመዝገብ የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ተቀባይነት አላገኘም።

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴው በቅርቡ ያስተላለፈው ብይን ታጂኪስታን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የጣለችው እገዳ ሕገ ወጥ እንደሆነ ይገልጻል። የታጂኪስታን መንግሥት ሃይማኖታዊ ማኅበሩ እንዲታገድም ሆነ በተደጋጋሚ ያቀረበው የምዝገባ ጥያቄ ውድቅ እንዲሆን “ምክንያት ብሎ ካቀረባቸው ነገሮች መካከል የትኛውም ቢሆን” ሚዛን እንደማይደፋ ኮሚቴው ገልጿል።

የታጂኪስታን መንግሥት፣ ሃይማኖታዊ ማኅበሩ እንደገና ለመመዝገብ ያቀረበውን ጥያቄ አለመቀበሉ ያስከተለውን ውጤት ኮሚቴው በመግለጫው አካትቷል፤ እነሱም “እስር፣ የቤት ብርበራ፣ ድብደባ፣ የሃይማኖታዊ ጽሑፎች መወረስ ብሎም [የአንድ] የይሖዋ ምሥክር ከአገር መባረር” ናቸው። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተፈጸመው ይህ አግባብ ያልሆነ ድርጊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ላይ የሃይማኖቱ ተከታዮች የተሰጣቸውን መብት የሚጥስ እንደሆነ ኮሚቴው አምኖበታል።

የ71 ዓመቱ ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ ከየካቲት 2019 አንስቶ በእስር ላይ ይገኛል

የታጂኪስታን መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮች ለመመዝገብ የሚያቀርቡትን ማመልከቻ ድጋሚ እንዲያጤነውና መብታቸው ለተጣሰባቸው ግለሰቦች የካሳ ክፍያ እንዲሰጥ ኮሚቴው ወስኗል። በተጨማሪም መንግሥት “ለወደፊቱ ተመሳሳይ የመብት ጥሰት እንዳይፈጸም አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ የመውሰድ ግዴታ እንዳለበት” ተጠቁሟል።

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴው ያሳለፈው ውሳኔ በ71 ዓመቱ ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ ፍርድ ላይም ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃል፤ ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ ሰላማዊ በሆነ መንገድ አምልኮውን በማከናወኑ ብቻ ከየካቲት 2019 ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኝ ይታወሳል። የታጂኪስታን ባለሥልጣናት ይህን ወንድም ለማሰር ሕጋዊ መሠረት ሊሆናቸው የሚችለው ብቸኛው ምክንያት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ ነው።

የኮሚቴው ውሳኔ በታጃኪስታን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የአምልኮ ነፃነት እንዲያገኙ በር ይከፍታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ‘ለምሥራቹ ለመሟገትና በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ’ ወንድሞች የሚያደርጉትን ያላሰለሰ ጥረት ይሖዋ እንዲባርክ ጸሎታችን ነው።—ፊልጵስዩስ 1:7