በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ የካቲት 2019 ከመታሰሩ በፊት

መጋቢት 4, 2021
ታጂኪስታን

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን በታጂኪስታን የታሰረው ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ እንዲፈታ ሊጠይቅ ነው

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን በታጂኪስታን የታሰረው ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ እንዲፈታ ሊጠይቅ ነው

የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ነፃነት ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት ኑሪ ተርኬል፣ በታጂኪስታን የታሰረው የ70 ዓመቱ ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ እንዲፈታ ሊጠይቁ መሆኑን የካቲት 24, 2021 ገለጹ፤ ኮሚሽነሩ ይህን የሚያደርጉት በኮሚሽኑ ሥር ባለው በሕሊናቸው ምክንያት የታሰሩ ሃይማኖታዊ እስረኞች ፕሮጀክት አማካኝነት ነው። ኮሚሽነር ተርኬል ባወጡት መግለጫ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ከባድ የጤና እክል ያለበት ይህ አረጋዊ፣ በእስረኛ በተጨናነቀና ባረጀ እስር ቤት ውስጥ ከ2019 ጀምሮ እየማቀቀ ነው፤ ይህ አረጋዊ ሰው ኢፍትሐዊ የሆነ የሰባት ዓመት ተኩል እስራት ተፈርዶበታል። እምነቱን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማራመዱ የተነሳ በግፍ የታሰረው ይህ የይሖዋ ምሥክር የተበየነበት ቅጣት እንደ ሞት ፍርድ ሊቆጠር ይችላል።”

ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ ባለቤቱን በሞት አጥቷል፤ ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ፣ የተደራጀ ወንጀል ቁጥጥር ዲፓርትመንት ባለሥልጣናት ጥር እና የካቲት 2019 ምርመራ ካደረጉባቸው በሰሜናዊ ታጂኪስታን የሚኖሩ 24 የይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ነው። የተደራጀ ወንጀል ቁጥጥር ዲፓርትመንት፣ ወንድም ሻሚል ካኪሞቭን በቁጥጥር ሥር ካዋለው በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት እንዴት እንደተዋቀረ በመጠየቅ ምርመራ አደረገበት።

ወንድም ሻሚል ካኪሞቭ በቁጥጥር ሥር ውሎ ለስምንት ሰዓት ያህል የቆየ ሲሆን በቅርቡ ቀዶ ሕክምና በማድረጉ ምክንያት ያስፈልገው የነበረውን የሕክምና እርዳታ ማግኘት አልቻለም። ወንድም ካኪሞቭ የደም ግፊትም አለበት። ፖሊሶች በመጨረሻ ወደ ቤቱ ሲወስዱትም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቹን፣ መጽሐፍ ቅዱሱን፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቹን እንዲሁም ፓስፖርቱን ወሰዱበት። ወንድም ካኪሞቭ ፓስፖርት ስለሌለው፣ ከቀዶ ሕክምና በኋላ ሕክምናውን ለመቀጠል የሚያስፈልገውን የጡረታ ገንዘብ መቀበል አልቻለም።

የካቲት 28, 2019 የኩጃንድ ከተማ ፍርድ ቤት ዳኛ ወንድም ካኪሞቭ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እስኪታይ ድረስ ማረፊያ ቤት እንዲቆይ ብይን አስተላለፉ። ወንድማችን ማረፊያ ቤት የሚቆይበት ጊዜ ርዝመት ሦስት ጊዜ ተራዝሟል። ምርመራው ሲካሄድም ሆነ በፍርድ ሂደቱ ወቅት ወንድም ካኪሞቭ ማረፊያ ቤት ቆይቷል።

መስከረም 10, 2019 ወንድም ካኪሞቭ የሰባት ዓመት ተኩል እስራት ተፈረደበት። ይሁንና ሐምሌ 4, 2020 የእስር ቤቱ አስተዳደር በታጂኪስታን የምሕረት ሕግ መሠረት የእስር ቤት ቆይታው በሁለት ዓመት ከሦስት ወር ከአስር ቀን እንደሚቀነስ ለወንድም ካኪሞቭ አሳወቀው። በመሆኑም ወንድማችን የሚፈታው ግንቦት 16, 2024 ይሆናል።

ይሖዋ፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በትዕግሥትና በደስታ እንዲጸኑ መርዳቱን እንደሚቀጥል እንተማመናለን።—መዝሙር 20:2