በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መጋቢት 21, 2023
ቶጎ

አዲስ ዓለም ትርጉም በካቢዬ ቋንቋ ወጣ

አዲስ ዓለም ትርጉም በካቢዬ ቋንቋ ወጣ

መጋቢት 12, 2023 አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በካቢዬ ቋንቋ ወጣ። የቤኒን ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዊልፍሪድ ሶሂንቶ ይህን ያበሰረው በካራ፣ ቶጎ በተደረገ ስብሰባ ላይ ነው፤ በፕሮግራሙ ላይ ከ2,959 በላይ ሰዎች ተገኝተዋል። a መጽሐፍ ቅዱሱ መውጣቱ እንደተነገረ የታተሙ ቅጂዎች የተሰራጩ ሲሆን ኤሌክትሮኒክ ቅጂዎችም ለተጠቃሚዎች ተለቅቀዋል።

ካቢዬ በዋነኝነት የሚነገረው በሰሜናዊ ቶጎ ነው። አጎራባች በሆኑት በቤኒን እና በጋናም ይነገራል። ካቢዬ፣ አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው።

በካራ፣ ቶጎ የሚገኘው የካቢዬ የርቀት የትርጉም ቢሮ

በካቢዬ ቋንቋ የተተረጎሙ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሶች አሉ፤ ሆኖም የአምላክን ስም መግባት ባለበት ቦታ ሁሉ ላይ እንዲገባ ያደረገው የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ ዓለም ትርጉም ነው። የአምላክን ስም የያዘ ሌላ የካቢዬ መጽሐፍ ቅዱስ ቢኖርም በዚህ ትርጉም ላይ ስሙ የሚገኘው ዘፀአት 3:15 ላይ ብቻ ነው።

ከተርጓሚዎቹ አንዱ አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ይህንን መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት እንድንችል ይሖዋ ሥራውን እየደገፈው እንደነበረ በግልጽ ማየት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱሱ በአገልግሎታችን ይጠቅመናል፤ በጉባኤ ስብሰባዎችም ላይ ቢሆን በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም በጣም አስደሳች ነው።”

ካቢዬ ተናጋሪ ወንድሞቻችን ‘የይሖዋን ስም ለማወደስ’ የሚያስችላቸውን ይህን ውድ ስጦታ በማግኘታቸው እኛም የደስታቸው ተካፋይ ነን።—መዝሙር 135:1

a በቶጎ የሚካሄደውን የስብከት እንቅስቃሴ የሚከታተለው የቤኒን ቅርንጫፍ ኮሚቴ ነው።